
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቃል ኪዳን ተሰጠች፣ ለምልክት ተቀመጠች፣ በነጻነት ኖረች፣ በክብር ትውለበለባለች፣ በልጆቿ ፍቅር ከፍ ትላለች፣ በልጆቿ ደምና አጥንት ትጸናለች፣ በጠላቶቿ ፊት ትከበራለች፣ ለተጨነቁ ሁሉ ተስፋና ምልክት ትኾናለች፤ በጨለማ ውስጥ ላሉ በብርሃን ተራራ ላይ ኾና ትታያለች፡፡
በስሟ የተራራቁት ይቀራረባሉ፣ በስሟ የተጣሉት ይታረቃሉ፣ በስሟ ከዳር ዳር ያሉት ይሰባሰባሉ፣ በስሟ ፍቅርን ያጸናሉ፣ አንድነትን ያጠናክራሉ፣ በስሟ ዘምተው በድል ይመለሳሉ፣ ክብሯን የነካባቸውን ድል ይመታሉ፣ በግፍ እግሩን ያነሳውን ይጥላሉ፣ በነበልባል ክንዳቸው ይደቁሳሉ፡፡
የጠላት መብዛት ከምትወለበለብበት ከፍታ ላይ አላወረዳትም፣ የቅኝ ገዥዎች ወጀብ አልጣላትም፣ የጦሩ መብዛት፣ የጎራዴው መበርከት ከክብሯ አላናወጻትም፣ በመከራ ዘመን ልጆቿን እያጸናች፣ በአንድነት እያስተሳሰረች፣ በጥላዋ ሥር እያሰባሰበች የገፋትን ሁሉ ትጥላለች፣ የነካኳትን ሁሉ ትቀጣለች፣ የደፈራትን ሁሉ እጅ ታስነሳለች እንጂ፡፡
በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ሠንደቅ ይከበራል፣ ለሠንደቅ እጅ ይነሳል፣ ለሠንደቅ ሁሉን ነገር ይሠጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሠንደቃቸው የሚመጣባቸውን አይታገሱም፣ ለሠንደቃቸው ሕይወታቸውንም ቢኾን አይሳሱም፣ ላብ በፈለገች ጊዜ ላባቸውን፣ ደም በፈለገች ጊዜ ደማቸውን፣ አጥንት በፈለገች ጊዜ አጥንታቸውን፣ ሕይወትም በፈለገች ጊዜ ሕይወታቸውን እየሠጡ ከሁሉም አልቀው አኑረዋታል፡፡
ሠንደቃቸው ለዘመናት በአንድነት ያኖረቻቸው የጋራ ክብራቸው፣ የጋራ መገለጫቸው፣ የጋራ ማንነታቸው ናትና አብዝተው ይወዷታል፣ አብዝተውም ይመኩባታል፡፡
በስሟ ይምሉባታል፣ በስሟ ዋስ ይጠሩባታል፣ በስሟ ቃል ኪዳን ያሥሩባታል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋን ሠንደቅ አብዝተው ከመውደዳቸው እና ከማክበራቸው የተነሳ የሠንደቋ ሥም በተጠራ ጊዜ ከጥልና ከጥላቻ ይርቃሉ፣ በሠንደቋ ስም አዋጅ በታወጀ ጊዜ እንደ ዓይን ጥቅሻ፣ እንደ ከንፈር ንክሻ በፍጥነት ይሰባሰባሉ፣ ስለ ፍቅሯና ክብሯ ተሰባስበው ትዕዛዝ ለመፈጸምና ለክብሯ ለመዋደቅ እየተማማሉ ትዕዛዝ ይጠብቃሉ፡፡ ትዕዛዝም በተሰጣቸው ጊዜ በደስታ እኔ እቀድም እኔ እቀድም እያሉ ለዘመቻ ይተማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ “በባንዲራው አምላክ” ተብሎ ከተገዘተ ሰው እጁን ለግጭት አያነሳም፣ ለበቀል ምላጭ አይስብም፡፡ በባንዲራው አምላክ ሲሉ እጅግ ከባድ እና ረቂቅ ነውና ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያውያን እጅግ ሕግ አክባሪዎች ከመኾናቸው የተነሳ በባንዲራው አምላክ ብቻ ሳይኾን “በንጉሡ አምላክ” ሲባሉም ግዝት ያከብራሉ፤ አታድርጉ የተባሉትን ሁሉ ይተዋሉ፡፡ ይህ የከበረ ሕጋቸው እና እሴታቸው ከዘመናት በፊት ጀምሮ የኖረ ነው፡፡
ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በተሰኘው መጽሐፋቸው “ኢትዮጵያዊያን ሀገር፣ ሕዝብና መንግሥት ኾነው መኖር ከጀመሩበት ጀምሮ ከኖኀ በውርስ የተቀበሉትን፣ ቀስተ ደመና ፈጣሪያቸው እንደ ቃል ኪዳኑ በእየልባቸው ጽላት ላይ ጽፎትና በእየልቡናቸው ውስጥ አሳድሮባቸው እርሱን አምላካቸውን በእውነት እና በመንፈስ ሲያመልኩበት ኖረዋል፡፡ እንዲህ እየኖሩ ሣሉ በኋላ ዘመን ለሕዝብ ማንነት መታወቂያና ለሀገር ምንነት መለያ የሚኾን ብሔራዊ እና መንግሥታዊ ምልክት አዘጋጅቶ ማውጣት አስፈላጊ የኾነበት ጊዜ ሲደርስ ሰው ሠራሽ ሠንደቅ ዓላማ መፈልሰፍ አላስፈለጋቸውም፤ ለዘመናት የጸናውን ማስቀጠል እንጂ።
ሠንደቃቸውን አክብረውና አስከብረው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ከዓመታት ወዲህ ግን ለሠንደቅ የሚሰጠው ክብር ቀንሷል፣ በሠንደቅ መማል፣ በሠንደቅ መገዘት፣ ግዝትንም ማክበር ላልቷል ይላሉ አበው፡፡
በደሴ ዙሪያ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪና የሽምግልና አዋቂ አሕመድ መኮንን በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያዊያን ለሠንደቅ ዓላማ ትልቅ ክብር አላቸው፣ ስለ ሠንደቅ ዓላማ ይማራሉ፣ ለሠንደቅ ዓላማ ክብር ይሠጣሉ፤ ለትልልቅ ሰዎችም ክብር ይሰጣሉ ይላሉ፡፡ የማኅበረሰብ ምልክት እና እሴት የኾኑ ጉዳዮችን የጣሰ ሰው ማኅበራዊ ቅጣት ይመጣበታል፡፡ ይሄን ስለሚያስብ በባንዲራ አምላክ ካልከው ከሚሄድበት ይቆማል፣ ለጥል ያነሳውን እጁን ያጥፋል ነው የሚሉት፡፡ የሠንደቅ ዓላማውን ክብር ከጣሰ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያስወግዛል፡፡
ሽማግሌን አለማክበርም በማኅበረሰቡ ዘንድ ታላቅ ነቀፌታ ያመጣል፡፡ በቀደመው ዘመን ሰዎች እየተደባደቡ “በባንዲራው አምላክ” ወይም “በንጉሡ አምላክ” ከተባሉ ገላጋይ መካከላቸው ሳይገባ ያቆማሉ፣ ይህ ሕግ አክባሪነትን፣ ለእሴት እና ማኅበረሰብ ላመነበት ነገር ተገዢነትን ያሳያል፡፡ አሁን ላይ መልካም እሴቶች አይሰበኩም፣ ለትውልዱ አይነገሩም፣ የማይጠቅሙ ያረጁ ያፈጁ ተደርገው ይቆጠራሉም ይላሉ፡፡
ሠንደቅ ዓላማ ማንነት፣ ምልክት፣ የቃል ኪዳን ስጦታ፣ ከደምና ከአጥንት ጋር የተዋሐደች ናት ተብሎ በሚታመንባት ሀገር፣ ባንዲራ ጨርቅ ነው እስከሚል አስተሳሰብ ወርደናልም ይላሉ፡፡ ለባንዲራ ክብር መስማማት ጠፍቷል፣ ሁሉም ባንዲራ ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ ሽምግልና አዋቂው ስለ አንዲት ሀገር ባንዲራ ሲናገሩ ለአንዲት ሀገር አንዲት ባንዲራ አለች፣ ያቺ ባንዲራ መሰባሰቢያ፣ በአንድ ጥላ ሥር ማገናኛ የኾነችውን ማጠናከር ሲገባ ሁሉም ራሱ ለፈጠረው ባንዲራ ያደላል፣ የጋራ የኾነችውን ችላ ይላል፡፡
ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ሰዎች ሠንደቅ ዓላማው ተሰቅሎ ሲውለበለብ ያለቅሳሉ፣ ይህም የሚኾነው ሠንደቅ ዓላማ ሀገርን ስለሚወክል፣ የሀገር ፍቅር መንፈስ ስላለው ነው ይላሉ፡፡ በሠንደቋ ውስጥ ያለውን የሀገር ፍቅር ማውሳት የተገባም ነው፡፡ ለነገሮች የምንሰጣቸው ግምት እየቀነሰ በሄደ ቁጥር ዋጋ እያስከፈሉን ይቀጥላሉ፡፡ የተፈጠረው የተሳሳተ ትርክትና ኾነ ተብሎ የተጫነው አስተሳሰብ የጋራ የኾነ ነገር እንዳይኖር እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
አንዱ ልሙትልሽ ይላታል፣ ሲኖር ጌጡ ያደርጋታል፣ ሲሞትም መቀበሪያዬ ትሁን ይላል፣ ሌላው ደግሞ ክብሯን፣ በውስጧ ያየችውን ምስጢሯን፣ የአንድነት ገመዷን፣ የሀገር ፍቅር መንፈሷን ረስቶ ጨርቅ ያደርጋታል፡፡ ሠንደቅ ዓላማን የአንዲት ሀገር የጋራ ምልክት፣ የአንድነት ገመድ እና የጋራ መሰባሰቢያ ጥላ አድርጎ መቁጠር ይገባልም ነው ያሉት፡፡
በወሎ ዪኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) ሠንደቅ ዓላማ ሕዝብን በአንድነት የሚያሰባስብ፣ በፍቅር የሚያስተሳስር፣ እንዳይለያይ የሚያገናኝ ነው ይላሉ፡፡ ለአብነት በዓድዋ ጦርነት አንደኛው ማስተሳሰሪያ ሠንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ሠንደቅ ዓላማ ዝም ብሎ ቀላል ነገር አይደለም፣ ሀገር የሚወከልበት፣ ሀገር የሚገለጽበት፣ ሕዝብ የሚሰባሰብበት፣ ማንነት የሚነገርበት ራሱ ሀገር ነው፤ ኢትዮጵያዊያን ዘለመናት ሠንደቃቸውን እንደ ምድራዊ ምልክታቸው ብቻ ሳይኾን በሰማይ የሠጣቸው የቃል ኪዳን ምልክት አድርገው ሲያምኑበትና ሲያከብሩት ኖረዋል ነው የሚሉት፡፡
በዓድዋ ላይ የተሸነፉትና ሌሎችም በኢትዮጵያ ላይ ቂማቸውን አይረሱም፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም በተነሱ ቁጥር የሚያነሱት ጉዳይ አንደኛው ሠንደቅ ዓላማ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያን እንድነት ጠብቆ ያቆዬ፣ ለጠላት እንዳይገዙ የሚያደርጋቸውና የሚያሳሰባቸው፣ ሠንደቅ ዓላማ እያለ ድል እንደማይኾኑ ስለሚያውቁ ለሠንደቅ ዓላማው ክብር እንዳይሠጥ የበዙ ነገሮችን መሸረባቸውንም ያነሳሉ፡፡
እነርሱ በሠጡት የተሳሳተ ትምህርትና ሴራ የሠንደቅ ዓላማ ክብር እንዲቀንስ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ የጋራ የኾነ ተረክ መፍጠር ግድ ይላል፣ የጋራ የኾነ ነገር የተበተነን ይሰበስባል፣ የሚለያየውን አንድ ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡
በወሎ ዪኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር ብርሃኑ ቦጋለ ነገሥታቱ በአምላክ ፈቃድ የተቀቡ እንደኾነ ስለሚታመን ስማቸው፣ ሥራቸውና ሕጋቸው ይከበራል፣ በስማቸው የተገዘተ ሰው ክፉ ነገር ለማድረግ አይሻም ነው የሚሉት፡፡ በንጉሡ አምላክ የተባለ ሰው ከእርምጃውም ይቆማል ይላሉ፡፡
በዚህ ዘመን ዴሞክራሲ በሚል ሰበብ ለዘመናት የተሠሩ እሴቶችና ሕጎች ተንደዋል፣ ተንቀዋል፣ ታላቅ ኾነው ሳለ እንደ ምንም ታይተዋል ነው የሚሉት፡፡ ዴሞክራሲን ከባሕል፣ ከእሴት፣ ከታሪክ፣ ከሃይማኖት ጋር መቃኘት ካልተቻለ እና ልቅ ከኾነ የነበረውን ያፈራርሳል፡፡ ቤተክህነት እና ቤተ መንግሥት ሀገርን በጋራ ይመሩባት በነበሩባት ሀገር ውስጥ የቀደመውን ሙሉ ለሙሉ መጣል የተገባ አይደለም ነው የሚሉት፡፡
ከንጉሣዊ ሥርዓት ወዲህ የመጡ ሥርዓቶች የትናንቱን የማውደምና የማፍረስ አባዜ ላይ መጠመዳቸው የጋራ ነገር እንዳይኖር እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በየዘመኑ የነበረው የሥርዓት መለዋወጥ ችግር ፈጥሯል፡፡ አሁን ይባስ ብሎ የጋራ ታሪክ ባይኖረን የጋራ ተስፋ አለን የሚል ሃሳብ እየመጣ ነውም ይላሉ፡፡ ሀገር፣ ባሕል፣ ታሪክና እሴት የሚሠራው በሰው ነው፣ በምክክር የጋራ መግባባት፣ የጋራ ታሪክ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሀገራት ጠንካራ ሀገር የመሠረቱት በጋራ መግባባት ነውም ይላሉ፡፡
አሁን ወጀብ ላይ ነው ያለነው፣ ወጀቡ እስኪያልፍ ድረስ ግፊት ይኖራል፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ላለችበት ሁኔታ ተዳርጋለች፣ አይቀርም አንድ ቀን ሁሉም መልካም ይኾናል፤ ችግሮችን በጥበብ በንግግር ማለፍ አለብን፣ ከዚያ በኋላ የጋራ መግባባትና የጋራ ማንነት ያለን እንኾናለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ስላለችበት ሁኔታ ሲናገሩ ኢትዮጵያ የታመመችው ፖለቲካው በመታመሙ ነው፣ፖለቲካው የግል ምጣኔ ሀብት ማመንጫ የኾነ የጉሮሮ ፖለቲካ ኾኗል፡፡ ፖለቲካው ለሀገር ክብር፣ ለሀገር ፍቅር ሲኾን ኢትዮጵያ ከሕመሟ ታገግማለች፣ ያጣችውን መልካም ነገርም ታገኛለች ነው የሚሉት፡፡ የግልን ጥቅም ለማሳካት ወደ ፖለቲካ መምጣት ለሀገር አደጋ ነው፣ ግን አምናለሁ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ መልካም ይኾናል ነው ያሉን፡፡
በማሰባሰቢያዋ ሠንደቅ ተሰባሰቡባት፣ በአንድነት ማሰሪያዋ ሠንደቅ አንድ ሁኑባት፣ በቃል ኪዳኗ ሠንደቅ ቃል ኪዳንን ጠብቁባት፣ ከሁሉ አስቀድማችሁ ጠብቋት፣ አስጠብቋት፣ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ አንድ ትኾናለች፣ ያን ጊዜ ሰላም በየጎዳናው በየደጁ ትትረፈረፋለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!