
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ታሪክን ለመጻፍ ሥነ-ጽሁፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የቀደመ ጥንታዊ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ታሪክ ጠገቧ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል እና የሥነ-ጽሑፍ እርሾ ባለቤት ብትኾንም ታሪክን በተገቢው መንገድ ከትቦ ለትውልድ በማስተላለፍ በኩል ግን ውስንነቶች እንደነበሩ ተደጋግሞ ይነሳል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር) ታሪክ ያለፈውን የሚነግር ብቻ ሳይኾን መጻዒውንም የሚያመላክት የትውልድ ቅብብሎሽ መስታውት ነው ይላሉ።
የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር አሰፋ ባልቻ በኢትዮጵያ ታሪክን እንደ አንድ የትምህርት መስክ መስጠት የተጀመረው በ1960ዎቹ አካባቢ እንደ ነበር ያነሳሉ። ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ድርሳናት ምንጫቸው አንድም ከቤተ ክህነት ወይም ከቤተ መንግሥት የመነጨ እንደነበር ብዙዎቹን የታሪክ ተመራማሪዎች ያስማማል።
ከ1960ዎቹ በፊት የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ የተጻፈ ታሪክ ቢኖር እንኳን በጣም ውስን ነው። የተጻፉት የኢትዮጵያም ኾነ የአህጉሪቷ ታሪኮች ምንጫቸው የውጭ ጸሐፊያን በመኾናቸው የራሳቸው የኾነ ጉድለት እና ውስንነት ሲኖርባቸው እንደሚስተዋል ነው የታሪክ ተመራማሪው የገለጹት።
እነዚህ በውጭ ጸሐፍት የተወጋጁ ጉድለት የበዛባቸው የታሪክ ማስረጃዎች እና መረጃውች ደግሞ በአብዛኛው ፀረ-የአንድነት መርዝ የተዘራባቸው መኾኑን የታሪክ ተመራማሪው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ እየከፈሉት ላለው የእርስ በእርስ ግጭት መነሻ ምክንያቶቹም እነዚሁ የተዛቡ ትርክቶች ውጤት ናቸው ሲሉ የሚስማሙት በርካቶች ናቸው።
በተለይም ደግሞ የጭቋኝ ተጨቋኝ ቅኝት፤ የገዳይ ተገዳ ይ ትርክት የአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ግብን የማሳካት ፍላጎት ባላቸው ቡድኖች ጭምር የተጻፉ ትርክቶች ኾነው በመዘራታቸው ግጭቶችን እና ውድመቶችን ሲያደርሱ ይስተዋላል።
“ታሪክ የማያቋርጥ ክስተት እስከኾነ ድረስ የግጭት መንስዔ ኾኖ አይውቅ፤ ሊኾንም አይገባም” የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው በኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ላይ የተቀራረብ የጋራ እውነት እና እምነት መያዝ ያስፈልጋል ይላሉ።
የሚስተዋሉ እና የተዛቡ የታሪክ አረዳዶችን ወደ ተቀራረበ አመለካከት እንዲመጡ ለማድረግ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር መቋቋሙን ዶክተር አሰፋ ገልጸዋል።
የማኅበሩ መቋቋም በስሜታዊነት እና በውሸት ትርክቶች ላይ ሙያው እና ልምዱ በሌላቸው ጸሐፊዎች በየመንደሩ እየታተሙ መንገድ ላይ የሚበተኑ ጽሑፎችን ያስቀራል።
ማኅበሩ እየጠነከረ ሲመጣም ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት መንስዔ ሊኾኑ የሚችሉ የበዳይ ተበዳይ ትርክቶች ይከስማሉ የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው አሁን የሚስተዋሉት አንዱ ሌላኛውን የሚመከትበት የተዛባ እይታ ችግሮችም ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን ታሪክን የሚቀበሉበት፣ የሚመክሩበት እና የሚከራከሩበት አውድም ከእልክ እና ስሜት ወጥቶ ሌላውን ለማዳመጥ፣ ለመረዳት እና ለአብሮነት በሚመች መልኩ መኾን አለበት ብለዋል። የሰለጠነ፣ ሳይንሳዊ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ አረዳድ በፖለቲከኞች፣ በወጣቶች እና በልሂቃን ዘንድ ሊኖር እንደሚገባም መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!