“በምሥራቅ ጎጃም ዞን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በተፈጠረባቸው ወረዳዎች ትምህርት ተጀምሯል” የዞኑ ትምህርት መምሪያ

43

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የ2016 የትምህርት ዘመን በወቅቱ እንዳይጀመር ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮ የቆየ መኾኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህን የሰላም ችግር ለመፍታት በተደረገው ርብርብ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ የትምህርት ሥራውን ለማስጀመር የተለያዩ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወን ተችሏል።

የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ካለባቸው ወረዳዎች መካከል በደጀን ወረዳ አሥተዳደር በሚገኙ አምስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራውም በይፋ ተጀምሯል።

አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሥራውንም የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች በወረዳው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ምልከታ አድገዋል። መምህራንና የትምህርት መሪዎች ተግባሩን በተደራጀ መንገድ እየፈጸሙ መኾኑም ተገልጿል።

ይህንን ተግባር ወደሌሎች ወረዳዎች እና ቀሪ ትምህርት ቤቶች ለማስፋት በቅንጅት እየተሠራ ነው ፤ በቅርቡ ተጨማሪ አምስት ወረዳዎች የመማር ማስተማር ሥራቸውን ማከናወን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የመምሪያ ኃላፊው ጌታሁን ፈንቴ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ እንደ ዞን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ633,000 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል ኀላፊው። በዞኑ የተፈጠረው የሰላም እጦት ግን የትምህርት ሥራውን ከመጉዳቱም በላይ በክልልና ሀገር አቀፍ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ነው ያሉት።

እንደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ጫናውን ለመቀነስና ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት ኃላፊው።

ወላጆችና መላ ሕዝብ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርታቸውን ያለስጋት እንዲከታተሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን አበሰሩ።
Next articleበሦስት ወራት ከዳያስፖራው ከ745 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ተሰብስቧል” የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት