
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ አብስረዋል።
አቶ አደም ፋራህ ለ2016/2017 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም የበጋ መስኖናና የመኸር ወቅት ሰብል ልማት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን ምላሽ ለመስጠት ጅቡቲ ወደብ ተገኝተው ወደ ሀገር ቤት የማጓጓዝ ሥራውን አብስረዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከግዥ ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ ባለው ሂደት ጠንካራ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥም የ13 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም የማጓጓዝ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ካለፈው ዓመት የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸርም በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በብዛት፣ በአነስተኛ ዋጋ እና በጥራት መግዛት እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ግዥ የተፈጸመበትን የአፈር ማዳበሪያም በተሳለጠ መንገድ በማጓጓዝ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ በማድረስ ምርታማነትን የበለጠ ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራው በይፋ መጀመሩን በመጠቆም፤ በወደብና ማጓጓዝ የሥራ ሂደቱ ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ለሚገኘው በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምሥጋና አቅርበዋል።
በግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪ የማጓጓዝ ሂደትን ለመጎብኘት ትናንት ምሽት ጅቡቲ መግባቱ የሚታወስ ነው።
ኢዜአ እንደዘገበው ልዑካን ቡድኑ ጅቡቲ አምቡሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ እና በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፣ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!