
አዲስ አበባ: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፍላጎት የወደብ ብቻ ሳይኾን የፍትሕም ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሠጡት ሳምንታዊ መግለጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰሞኑን ከሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር ወሳኝ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሀገሪቷ መሪዎች የተለያዩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በማከናወን ለምጣኔ ሃብታዊ ዲፕሎማሲ መሠረት የኾኑ ሥራዎችን አከናውነዋል ተብሏል።
በሦስት ወራት 48 የኢንቨስትመንት መድረክ ላይ በመሳተፍ ሀገሪቱን የማሥተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል። ይህ የማስተዋወቅ ሥራ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሩቅ ምስራቅ እና በአሜሪካ ላይ የተካሄደ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በመድረኮቹ ላይ ምጣኔ ሃብታዊ ሽርክና ሥራ ላይም ሥምምነት ተደርጓል።
በ2016 ዓ.ም ዲፕሎማሲውን ወደ መደበኛ መንገድ በመመለስ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። በእውቀት እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሠሩ ሥራዎች የሽግግር ዲፕሎማሲው አካል አድርጎ ተሠርቷል ብለዋል።
ከቀይ ባሕር እና አካባቢያዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጥያቄ የተነሳላቸው አምባሳደር መለስ ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሃሳብ አሥፈላጊ እና የረዥም ጊዜ ጥያቄም ጭምር ነው ብለዋል።
ሃሳቡ በመገናኛ ብዙኀን እየተነሳ ያለበት ሁኔታ ትክክል አይደለም ያሉት አምባሳደር መለስ ዓለም የኢትዮጵያን ፍላጎት በወደብ ልክ ብቻ አሳንሶ መመልከት ጠቃሚ አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ የባሕር በር እና የፍትሕ ጥያቄ ጭምር ነው ብለዋል። ሥለዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ ጉዳይ ትላንትም ሲሠራ ነበር ዛሬም ይሠራል ነው ያሉት። የቀጣናው ሌሎች ሀገራት ተሳታፊ ኾነው ሳለ ኢትዮጵያ ገለልተኛ ኾና የምትቀጥልበት መንገድ የለም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!