
አዲስ አበባ: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 25ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ለዘላቂ የጤና ልማት በሚል መሪ መልእክት ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ እንደተናገሩት በከተማ አሥተዳደሩ በ19 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ጥገና ህክምና መስጠት ተችሏል። በ28 ጤና ጣቢያዎችና 9 ሆስፒታሎች የማስፋፊያ እና የእድሳት ሥራ ተሠርቷል።
በጤና መድኅን ሽፋን ከ271 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል።
ለበርካታ ማኅበረሰብ ክፍሎችም የከተማ አሥተዳደሩ ወጫቸውን መሸፈን ችሏል ብለዋል ኀላፊው።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጤናማ ዜጋ የልማትና ምርታማነት ቁልፍ በመኾኑ ጤናማ ማኅበረሰብን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከንቲባዋ እንዳነሱት በጤናው ዘርፍ በአዲስ አበባ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የቀዳማይ ልጅነት ጤናማ አእምሯዊና አካላዊ ብቃት ያላቸው ዜጎችን የመፍጠር ሥራ በከተማው በልዩ ሁኔታ እየተተገበረ ነው።
የጤናው ዘርፍ የልህቀት ማእከል ግንባታ ሥራ ለጤናው ዘርፍ ምቹ ኹኔታን ከመፍጠር አንፃር 8 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያና እድሳት እና ሁለት አዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። የጤና መድኅን ሥራዎችም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
አሁንም ከፍተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገሩም ተገምግሟል ብለዋል።
የዜጎችን ጤና ለማሻሻል በከተማው የማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ፣ የከተማ ግብርና እና መሰል ሥራዎችን ለጤናው ዘርፍ እንደ ግብዓት ይኾን ዘንድ እየተሠራ ነው። ከተማዋን ከትንባሆ ነፃ የኾነች ለማድረግ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር እየተሠራም ነው ብለዋል።
አዲስ አበባን በጤናው ዘርፍ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የቀሩትን ክፍተቶች መገምገምና ስኬቶችን ማጋራት እንዲሁም ክፍተቶችን መሙላት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በተያዘው ዓመት እና በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚተገበሩ የጤና ዘርፍ የመካከለኛው ጊዜ የጤና ልማትና ማሻሻያ ሥራዎች ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ የተጀመረበት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ የጤናው ዘርፍ ጠንካራና የማይበገር የጤና ሥርዓትን መተግበርና ጠንካራ ፋይናንስ ለመፍጠር በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ድንገተኛ የጤና ምላሽ ፣ በጦርነትና ግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ለነዋሪዎችም አስቸኳይ የጤና ምላሽ እና ድጋፍ የመስጠት ሥራዎች በትኩረት የሚሠሩ እንደኾኑም ዶክተር ሊያ አብራተርተዋል፡፡
መድረኩን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርና ጤና ሚኒስቴር በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡ በመድረኩም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣ የክልል ጤና ቢሮ ኀላፊዎች ፣ የጤና ተቋማት ኀላፊዎች ፣ አጋር አካላትና ሌሎችም ታድመውበታል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!