
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም በሁሉም” ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል። ክልሉ ላለፉት ወራት በገጠሙት የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።
በምክክር መድረኩ ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ የሰላም እና የልማት ኹኔታ ለውይይት ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በክልሉና በከተማዋ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ ልማታችን ወደኃላ የተጎተተ መኾኑን ተረድተን ለሰላም መጠበቅ ልንሠራ ይገባል ያሉት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዮህ አቡሀይ የከተማዋ ሕዝብ ሕግ አዋቂ ነው እና በሕግ አግባብ ችግሮቹ እንዲፈቱ ሊጠይቅ ይገባል ብለዋል።
ውይይቱ ከተማችን ጎንደር ያሉባትን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት በሰከነ መንገድ በነፃ ሃሳብ መነጋገርን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል ከንቲባ ባዩህ።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የክልሉን ሕዝብ ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ዳርጎታል።
ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ለዘመናት በአብሮነት የሠራ ሕዝብ ከጋጠመው የሰላም እጦት በፍጥነት መውጣት አይከብደውም” ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ችግሮቻችን በውይይት ፈትተን ወደ ክልሉ ልማት እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ፊታችንን ማዞር ይጠበቅብናል ብለዋል።
“ሰላም ለሁሉም በሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ በተጀመረው የምክክር መድረክ ላይ ከጎንደር እና አካባቢው የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ናቸው። የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዮህ አቡሀይ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝዋል።
ዘጋቢ፦ መሠረት ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!