“ጥሩ ተሸናፊዎች ከመጥፎ አሸናፊዎች የበለጠ ክብር አላቸው” ፊፋ

54

ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በርካታ የሥነ ምግባር ሕጎች አሉት፡፡ ከሕጎቹ አንዱ የእግር ኳስ የመጫዎቻ ሜዳዎች ሰላማዊ ብቻ መኾን እንዳለባቸው ግዴታ ያስቀምጣል።

ሰላማዊ የእግር ኳስ ጨዋታ ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን የእህትማማችነት እና ወንድማማችነት መንፈስ ሊያጠናክር እንደሚገባው ፊፋ ደንግጓል፡፡

በፊፋ ሕግ መሰረት አንድ ተጫዋች ወይም ክለብ የሚጫወተው ለማሸነፍ ነው፡፡ ነገር ግን ሽንፈት ሲያጋጥም ተሸናፊው ክለብና ደጋፊዎች በክብር እንዲቀበሉት ሕጉ በአጽንኦት ያስገድዳል፡፡

የጨዋታውን ሕግ ያላከበረ ተጫዋች፣ ዳኛ እና ተመልካች ሲያጋጥም መቅጣት የግድ ነው፡፡ “ጥሩ ተሸናፊዎች ከመጥፎ አሸናፊዎች የበለጠ ክብር ያገኛሉ” ይላል ፊፋ በሥነ ምግባር ሕግ መመሪያው ።

የፊፋ አባል ሀገራት ደግሞ የፊፋን ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያም የፊፋ አባል ሀገር ናት፡፡ ታዲያ የሀገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በፊፋ የሥነ ምግባር ሕግ መሰረት እየተቃኙ ይሆን? እንቀጥል…
በኢትዮጵያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሲኖር የአንዳንድ ክለብ ደጋፊዎች የክለባቸውን መለያ ለብሰው የተቃራኒ ክለብ ተጫዋቾችን ስም እየጠሩ በአጸያፊ ቃላት ሲሸነቁጡ መደመጥ እየተለመደ ነው፡፡

አልፎ አልፎም የአንዱ ክለብ ተመልካች የሌላውን ክለብ ተመልካች ድንጋይ ወረውሮ ሲፈነክት፣ በቡጢ ሲነርት እና በጭንቅላቱ ሲገጭ መመልከት አዲስ ክስተት አይደለም፡፡

አቶ ብርሃኑ ሙላቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት የእግር ኳስ ጨዋታ በሚኖርበት ወቅት ስታዲየም ቀርተው አያውቁም፡፡ ሜዳ ገብተው በውብ ጨዋታ፣ በማራኪ የደጋፊዎች ዝማሬ እና ትርዒት ተዝናንተው በሰላም መመለስ ነበር ተስፋቸው፡፡

“ይሁንና” ይላሉ አቶ ብርሃኑ “በኢትዮጵያ የፕሪሚየር ሊግ የ2016 መርሐ ግብር ስታዲየም የእግር ኳስ መጫዎቻ ሳይኾን የድብድብ አደባባይ፤ የድንጋይ ውርዋሮ መለማመጃ ፤ የጉልበት መፈተሻ፤ የስድብ ናዳ ማውረጃ መድረክ እየመሰለ ነው። ስለዚህ አወዳዳሪው ክፍል ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን እንዲገስጹ ማድረግ አለበት” ብለዋል፡፡

ማቴክ መንበሩ የሰውልክ የቢሸፍቱ ከተማ ነዋሪና የአየር ኃይል ባልደረባ ናቸው፡፡ “በየጨዋታው የምንመለከተው ረብሻ ወደ ሜዳ እንዳንመጣ እያደረገን ነው፤ ደግሞ የሀገር ገጽታን ያበላሻል” በማለት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

በአንድ ጨዋታ የሲዳማ ቡና አምስት ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ መመልከታቸው የአስተያየት ሰጪዎችን ሃሳብ እውነትነት ያስረግጣል፡፡ እናም የሀገሪቱን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ‘ጤና ማጣት’ የዘርፉን ባለድርሻዎች ሁሉ ቆም ብለው እንዲያስቡበት ያስገድዳል ፡፡

ለአብነት ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዳኛን እና የተጋጣሚን ቡድን ተጫዋቾች በአፀያፊ ስደብ ‘ሲጋረፉ’ ተሰምተዋል፡፡ የወንበር ስብርባሪ ወደ ሜዳ ሲወረውሩም በተንቀሳቃሽ ምስል ዓለም ሳይቀር ተመልክቷል፡፡

የሀድያ ሆሳዕና ቡድን የክለቡን ዓርማ የለበሱ ደጋፊዎችም ወደ ሜዳ ድንጋይ ሲወረውሩ አይተናል፡፡ ሜዳውንም በረብሻ ሲንጡ ከንፈራችንን በቁጭት በተቆርቋሪነት ነክሰናል፡፡ የወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ ደጋፊዎችም የሀድያ ሆሳዕናን ስህተት ደግመውታል፡፡

በመኾኑም ሰላማዊ የስፖርት ቤተሰቦች “ኧረ! ምነው ሀይ ባይ ጠፋ? ጉዳዩ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ ሊባል ይገባዋል” እያሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አመራርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ጥፋት ሪፖርት መርምሯል፡፡

በዚህም መሰረት የክለብ መለያ የለበሱ ደጋፊዎች ዳኞችን እና የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በአፀያፊ ስድብ መሸንቆጣቸውን አረጋግጧል ፡፡ ስለኾነም ክለቡ እና የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት በዲሲፕሊን መመሪያው መሠረት ክለቦችን በገንዘብ ቀጥቷል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት አበረከተ።
Next articleኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳንን በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር ስምምነት ላይ ተደረሰ።