
ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2015 የትምህርት ዘመን በክልል አቀፍ እና በሀገር አቀፍ በተመዘገቡት የትምህርት ውጤቶች ላይ ከባላድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በዉይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ በ2015 የትምህርት ዘመን ከተፈተኑ 6 ሺህ 869 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 73 በመቶ የሚኾኑት ወደ ቀጣዩ ክፍል አልፈዋል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሔደው የ12ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ በ20 ከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 10 ነጥብ 3 በመቶ የሚኾኑት ተፈታኞች ማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንድ የመንግሥት እና አንድ የግል ትምህርት ቤት ላይ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ አለመገኘቱን በድክመት አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በከተማ አሥተዳደሩ ክልላዊና ሀገራዊ ፈተናን በስኬት ፈጽመው ጥሩ ውጤት ላመጡ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።
የባሕር ዳር ስቲም ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ውጤት በማብቃትም ትልቅ እውቅና ተስጥቶታል።
በእውቅና ሥነ ሥርዓቱም የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተገኝተዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሁን በከተማ አሥተዳደሩ የተገኘው ውጤት በቀጣይ ለሚከናወኑ የትምህርት ሥራዎች ትልቅ ማሳያ መኾኑንም ተናግረዋል።
ተማሪዎች ሀገር ተረካቢ እና ትውልድን የሚያስቀጥሉ በመኾናቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የትውልድ ግንባታ ሥራው ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተማሪ እምነት ሃብታሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል ፈተና 618 በማምጣት በከተማ አሥተዳደሩ የሜዳሊያ ተሸላሚ መኾን ችላለች።
ተማሪ እምነት በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሶፍት ዌር ምህንድስና ትምህርት በማጥናት በሀገሪቱ ያለውን የቴክኖሎጂ ክፍተት ችግር ለመፍታት ታላሚ አድርጋ እንደምትሥራ ለአሚኮ ተናግራለች፡፡
ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ እና ከታች ባለው የትምህርት ደረጃ መሠረት ከተጣለ በእውቀት የካበተ ትውልድን መፍጠር እንደሚቻልም ተናግራለች።
ዘጋቢ፡- አዲሱ ተስፋየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!