“የጤናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት የመጨረሻ ግቡ የዜጎችን ጤና ማሻሻል ነው” ጤና ሚኒስቴር

46

አዲስ አበባ: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 25ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔን አስመልክቶ በተመረጡ የጤና ተቋማት ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል።

የጉብኝቱ ዓላማ የጤና ተቋማቱ ዲጂታላይዝድ የመረጃ አያያዝና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ልምድ ለመለዋወጥ ነው ተብሏል።

25ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ “ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ለዘላቂ የጤና ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 21 እስከ 23/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጉባዔው የጤና ሚኒስቴር በዓመቱ የሠራቸውን ሥራዎች የሚገመግምበት፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት የሠሯቸውን ሥራዎች በጋራ የሚገመግሙበት እና ቀጣይ አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ይኾናል ተብሏል።

የዚህ አካል የኾነው የጤና ተቋማት የአገልገሎት አሰጣጥ ልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ጉብኝት በተመረጡ የጤና ተቋማት እየተካሄደ ነው።

ጉብኝቱን የጤና ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎች፣ የክልል የጤና ቢሮዎች፣ የጤና ጣቢያ እና ሆስፒታሎች በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት እና ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተከፋፍለው ነው እያካሄዱ የሚገኙት።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በመሩት ቡድን የአበበች ጎበና የእናቶች እና ሕጻናት ሆስፒታል እንዲሁም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ጤና ጣቢያ ተጎብኝተዋል።

ተቋማቱ የወረቀት ንክኪን ያሰወገደ ዲጂታላይዝ የጤና መረጃ ሥርዓት፣ ለኅብረተሰቡ ቅርብ የኾነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ሥርዓት እና የቅድመ ልጅነት የጤና ክብካቤ አገልግሎት ያለበትን ደረጃ ማየት እንዲሁም ተቋማት እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት እና በሀገሪቱ የሚሰፋበትን ዓላማ ይዞ ተካሂዷል።

በዚህም ተቋማቱ የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ደረጃ ላይ መኾናቸውን አይተናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት የሚደረገው ነገር የመጨረሻ ግቡ የዜጎችን ጤና ማሻሻል ነው ብለዋል።

በመኾኑም መረጃዎች ለውሳኔ ሰጭነት ያላቸውን ሚና በመረዳት ወረቀት አልባ የጤና ሥርዓትን በአግባቡ በመዘርጋት እና በመላ ሀገሪቱ በማስፋት በኩል ተቋማት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም መደገፍ የሚገባውን እንደሚደግፍም ዶክተር አየለ አረጋግጠዋል።

የቅድመ ልጅነት ጤና ክብካቤ ሥራውም የልጆችን ከጽንሰት እስከ ስድስት ዓመት ያለውን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት የተሻለ እንዲኾን የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠል እና ማስፋት ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ክልል ወደቀደመ ሰላሙ ሲመለስ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች በጥናት ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት አበረከተ።