አማራ ክልል ወደቀደመ ሰላሙ ሲመለስ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች በጥናት ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

51

አዲስ አበባ: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የግብዓት እጥረት በማጋጠሙ በምዕራብ አማራ አካባቢ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሥራ ማቆማቸው ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በአማራ ክልል በተፈጠረው አለመረጋጋት በረካታ ኢንዱስትሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይም አበባ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የደረሰው ውድመት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር የሚነጻጸር አይደለም ብለዋል።

በክልሉ የኢንተርኔት መቋረጥ፣ የኃይል እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት እጥረት እና ምርትን ለገበያ ማቅረብ አለመቻል በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ የወደሙ እና በከፊል ጉዳት የደረሰባቸው አምራች ኢንዱሰትሪዎች መኖራቸውን የገለጹት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ “ክልሉ ወደቀደመ ሰላሙ ሲመለስ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች በጥናት ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በ2023 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትሰበስባለች ተብሎ ይጠበቃል” የአፍሪካ ልማት ባንክ
Next article“የጤናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት የመጨረሻ ግቡ የዜጎችን ጤና ማሻሻል ነው” ጤና ሚኒስቴር