“ኢትዮጵያ በ2023 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትሰበስባለች ተብሎ ይጠበቃል” የአፍሪካ ልማት ባንክ

99

ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች ሲሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና (ዶ.ር) ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ የዓለም የምግብ ሽልማት ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የስንዴ ምርት ስኬታማ ጉዞ አድንቀዋል።

በሀገሪቱ የስንዴ ምርትን እ.ኤ.አ በ2022/23 የምርት ዘመን ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል። በሄክታር የሚገኘውን የስንዴ ምርትም ከሁለት ቶን ወደ አራት ቶን አድጓል ሲሉም ዶክተር አኪንዉሚ አዴሲና ተናግረዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት “ኢትዮጵያ በ2023 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትሰበስባለች ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

በ2018/19 የምርት ዘመን በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሲለማ የነበረውን የስንዴ ምርት በ2022/23 የምርት ዘመን ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ መቻሉንም አንስተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የግብርና ቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያን በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ጥረት ለማገዝ ከ100 ሺህ ቶን በላይ ድርቅን ተቋቁሞ ምርት መስጠት የሚችል ምርጥ ዘር ማቅረቡን ጠቁመዋል።

በውይይቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል።

ከመርሐ ግብሩ ጎን ለጎን ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በርካታ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ኢፕድ በዘገባው አስታውሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” የአበውን ብሂል መያዝ ይጠቅማል ፣ ከችግርም ያወጣል”
Next articleአማራ ክልል ወደቀደመ ሰላሙ ሲመለስ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች በጥናት ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር