
ደሴ፡ ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አበው ጥል የሚሻርባቸው፣ ፍቅር የሚጸናባቸው፣ ሰላም የሚሰፍንባቸው፣ አንድነት እንደ ዓለት የሚጸናባቸው፣ ከራስ በላይ ማሰብ የሚጎለብትባቸው፣ መለያየት የሚጠፋባቸው፣ ስንፍና የሚወገዝባቸው፣ ራስ ወዳድነት የሚነቀፍባቸው፣ ጽናት የሚሰበክባቸው፣ ታታሪነት የሚነገርባቸው፣ እንግዳ ተቀባይነት የሚገለጽባቸው እልፍ እሴቶችን ሠርተዋል፣ በእሴቶቻቸው አማካኝነት ጽኑ ማኅበራዊ ሥርዓት መሥርተዋል። በሠሩት ጽኑ እሴት የተከበረች ሀገር ከተወደደች ሠንደቅ ጋር አቆይተዋል።
ሀገርን ለማክበር፣ ሠንደቅን ለማፍቀር፣ ስለ ሀገር በአንድነት ለማበር የሚያስችሉ ብሂሎችን ፈጥረዋል፣ በፈጠሯቸው ብሂሎቻቸው አማካኝነት ሰላምና ፍቅርን ገንብተዋል። የአበውን ብሂል መያዝ ይጠቅማል፣ የችግርን ዘመን ያሻግራሉ፣ የፈተናን ወቅት ያሳልፋሉ። እነሱ በብሂሎቻቸው መከራውን ተሻግረዋል፣ ጥልና ጥላቻን ሽረዋል፣ ፍቅርና አንድነትን አጽንተዋልና።
ብሂሎችን የያዘ ትውልድ የነገር ውል አይጠፋበትም፣ የችግር መፍቻው መንገድ አይዘጋበትም፣ የሰላም በሩ አይከረቸምበትም፣ የፍቅርና የአንድነት ማሠሪያው አይላላበትም። ብሂሎችን የያዘ ትወልድ ትናንቱን ያውቃል፣ ዛሬውን ያመቻቻል፣ ነገውን ያሳምራል፣ አንድነቱን ያዳብራል፣ የችግሮች መፍቻ መንገዶችን ያስተካክላል። ብሂሎችን የተወ ትወልድ ትናንቱ ይጠፋበታል፣ ዛሬው ይበላሽበታል፣ ነገውን ማሳመርና መተንበይ ይሳነዋል።
በደሴ ዙሪያ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪና ሽምግልና አዋቂ አሕመድ መኮንን ማኅበራዊ እሴቶች አንድ ማኅበረሰብ ለረጅም ጊዜ በውስጡ ተቀብሏቸው፣ የሚተዳደርባቸው፣ የሚረዳዳባቸው፣ ይጠቅሙኛል ብሎ የያዛቸው፣ ለዘመናት ተሳስሮ የኖረባቸው ናቸው ይላሉ። ማኅበራዊ እሴቶች በመረዳዳት ፣ እንግዳ በመቀበል፣ ችግርን በጋራ በማለፍ መልኩ የሚገለጹ የሕዝብን ጠንካራ አንድነት የሚጠብቁ ናቸው።
ማኅበራዊ እሴቶች ከዘመን ዘመን የተሸጋገሩ መልካም ሕጎች ናቸውም ይሏቸዋል። ማኅበራዊ እሴቶች የሚፈጥሯቸው እና የሚኖሯቸው የምስጢር ሃሳብ ነው፣ የሰው ልጅ አስተሳሰቡን ለገዛው ነገር ይገዛል፣ ሕግጋቱን ይፈጽማል፣ ማኀበራዊ እሴቶች አንድን ማኅበረሰብ በአንድነት ፣ በእኩልነት የሚያገለግሉ ቅቡልነት ያላቸው ናቸው ይሏቸዋል። ሁሉንም ግጭቶች የሚፈቱ፣ ሰላምን የሚያመጡ በርካታ እሴቶች አሉ። አበው ሽማግሌ የማይሰፋው የለም እንዲሉ ለየትኛውም ችግር መፍትሔ አላቸው፣ የገዘፈን ችግር አኮስምነው፣ የገዘፈ ፍቅርና ሰላም ይፈጥራሉ።
ኢትዮጵያዊያን ደም የሚያደርቁበት፣ የተጋደሉትን የሚያስታርቁበት እሴት አላቸው። ከማኅበረሰቡ የሚያፈነግጥ በማኅበራዊ ሕጎች አማካኝነት ይቀጣል፣ ይገሰጻል፣ ሕጎችን ካላከበረ ከማኅበረሰቡ እስከ መገለል የሚደርሱ ቅጣቶች ይጠብቁታል፣ የማኅበራዊ እሴቶች መኖር ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው።
ማኅበራዊ እሴቶች ትውልድ ከትውልድ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋሉ፣ ታሪክን ያቆያሉ፣ ለመጪው ትውልድ ማስተማሪያ ይሆናሉ። ማኅበረሰብ አብረው የማያስኖሩ ድርጊቶችን ያወግዛል፣ ይሄን በማድረጉም ነው ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ጸንተው የኖሩት ነው የሚሉት። መተሳሰብ እንዲኖር፣ አንድነት እንዲጠነክር፣ በችግር መረዳዳት የሚፈጠረው በማኅበራዊ እሴቶች አማካኝነት ነው ይላሉ። ማኅበራዊ እሴቶች ለሰላም ግንባታ ከፍተኛ ሚና ያላቸውም ናቸው ይሏቸዋል።
የሰው ልጅ ሕይወት እንዲቀጥል ፣ ንብረት እንዳይወድም፣ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ፣ ክብሯን ጠብቃ እንድትሸጋገር ማኅበራዊ እሴቶች ሚናቸው ላቅ ያለ ነው። ማኅበራዊ እሴቶች መለያ ማንነት እና ጌጦች ናቸውም ብለዋቸዋል።
ወደድንም ጠላንም ማኅበራዊ እሴቶች እዚህ አድርሰውናል ፣ ወደፊትም ያስቀጥሉናል፣ ልንጠብቃቸውም ይገባል ነው ያሉት። ትውልድ ከትውልድ እንዲሸጋገር ያደረጉ ማኅበራዊ እሴቶች መኾናቸውንም ይገልፃሉ። መልካም እሴቶችን የሚጎዱ፣ የሚያቀዛቅዙ፣ ክብራቸውን የሚቀንሱ አካሄዶች እየተፈጠሩ መኾናቸውንም አስታውሰዋል። በማኅበራዊ እሴቶች አለመገዛት ፣ ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን ያለ ማክበር ችግር እየተፈጠረ መኾኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያዊያን አንደኛው መልካም እሴት ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው፣ በኢትዮጵያ ግጭቶች እየተባባሱ ያሉትም እሴቶችን በአግባቡ ባለመጠቀማችን ነው። ሰው በሰውነቱ ብቻ መከበር አለበት፣ የእኔ የተባለው ሁሉ ሁልጊዜ ትክክል፤ የእኔ ያልኾነው ሁሉ ሁልጊዜ ስህተት ነው ብሎ ማሰብ ልክ አይደለምም ይላሉ።
ማኅበራዊ እሴቶችን ለማጠናከር ሁሉም ድርሻ አለበት ነው የሚሉት። ማኅበራዊ እሴቶች ሲጠናከሩ ጠንካራ አንድነት እና ፍቅር ይኖራል። ማኅበራዊ እሴቶች ጠንካራ ሥርዓት አላቸው፣ የሃይማኖት አባቶች ጥልን የማድረቅ ኀይል አላቸው፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖትን ያከብራሉና፣ ይህ እንዲኾን ደግሞ እሴትን መጠበቅ ግድ ይላል ነው ያሉት። ችግሮችን በሰማያዊ መንገድ ስለ መፍታት ሲናገሩ ትልልቅ ሽማግሌዎች እና ሽምግልናዎች አሉን፣ በንግግር የማይፈታ የለም፣ ሽማግሌዎችን የሃይማኖት አባቶችን ማክበር ፍቅርን ያመጣል፣ ግጭትን ያጠፋል ነው ያሉት። ሽምግልና አዋቂው ችግርን ስለ መፍታት ሲናገሩ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት፣ በንግግር መፍታት ይገባል፣ እስካሁን ያቆዩንን የችግር መፍቻ መንገዶች ብንጠቀም እናተርፋለን እንጂ አንከስርም፣ ሰው ቁጭ ብሎ የእውነት ቢነጋገር ሕይወት ከመጥፋት፣ ንብረት ከመውደም ይድናል።
መልካም እሴቶችን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ትወልድን በሚገባ መግራት ፣ መልካም ነገር ማውረስ ይገባል ነው ያሉት። ሀገር ሳለች መመካከር እና መነጋገር ይገባል፣ ሀገር ከሌሎች ሁሉም ይቀራልና። ሀገር ላለመጉዳት መነጋገር፣ መመካከር፣ መከባበር ወሳኝ ጉዳይ ነውና።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!