“የሥማርት ፕሮጀክት ሲተገበር ባሕር ዳር ለነዋሪዎቿ ምቹ እና በዓለም ታዋቂ የጎብኝዎች መዳረሻ ከተማ ትኾናለች” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

33

ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በቅርቡ ”ስማርት ባሕር ዳር” የተሰኘ ዘርፈ ብዙ የልማት ፕሮጀክት በከተማዋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

”በኔ የሥራ ዘመን የባሕር ዳር ከተማ በዓለም ከሚገኙ ተመራጭ ከተሞች ተወዳዳሪ፣ ምርጥ የኢንዱስትሪ እና የቱሪስት መዳረሻ ኾና ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል። ለዚኽም የተጣለውን መሠረት ማሥፋፋት፣ አዳዲስ መሠረቶችን ለመጣል እና ለመገንባት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ”ስማርት ባሕር ዳር” ፕሮጀክት የከተማዋ ነዋሪዎች መረጃ በቀላሉ የሚያገኙባት፣ የሥራ ፈጣሪነት ክሕሎት የተሥፋፋባት እና የሁሉም አገልግሎት አሠጣጥ ዲጂታላይዝድ የሚኾንባት ከተማ ለማድረግ እየሠሩ መኾኑን አብራርተዋል። ፕሮጀክቱ የሀገር ሃብት ለትውልድ እንዲተላለፉ እና እንዲያገለግሉ አድርጎ መሥራት ዓላማ ያለው ነውም ብለዋል።

ባሕር ዳር ከተማ ደኅንነቷ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ ከተማ እና ጎብኚዎች የሚመላለሱባት እንድትኾን አቅደን እንሠራለን ብለዋል። ኅብረተሰቡም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

ባጋጠሙት ወቅታዊ የሰላም ችግሮች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማጋጠሙን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኢንዱሥትሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ግብዓቶች ስላልገቡላቸው እንዲሁም ምርቶቻቸውን ማስወጣት ስላልቻሉ ሥራ ማቆማቸውን ገልጸዋል። ስለኾነም ሰራተኞቻቸውን እስከመበተን እና ማሰናበት መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመልዕክታቸው ”የሰላም እጦቱ ድጋሚ እንዳይከሰት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዳይደናቀፉ ኹሉም ሰው የከተማዋ ዘላቂ ሰላም ባለቤት እንዲኾን ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ወደ ቀደመ ፍትሕ የማረጋገጥ ሥራ እንዲገቡ የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መኾኑን ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።
Next article” የአበውን ብሂል መያዝ ይጠቅማል ፣ ከችግርም ያወጣል”