ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ወደ ቀደመ ፍትሕ የማረጋገጥ ሥራ እንዲገቡ የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መኾኑን ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

40

ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾናቸው በተገልጋዮች ዘንድ ቅቡል ናቸው። በየአካባቢው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እና ቅራኔዎችን የመፍታት አቅማቸው ከፍተኛ ነው።

የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየት እና በመከላከል ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው ገጠራማው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምን በማስፈን የማይተካ ሚና አላቸው።

በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በመለየት አጥፊውን በመቅጣት እና ተበዳዩን በማስካስ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ማኅበረሰባዊ መሠረት ያላቸው ቢኾኑም አሁን ላይ አስተዋጾአቸው እየቀነሰ መምጣቱን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ነባራዊ ኹኔታ ሕግ በአግባቡ የሚተገበርበት አለመኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያገኙ እና የሚተገበሩ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ እሳቤ ነጸብራቅ በመኾኑ ሀገርን መሥራት እና ማኅበረሰብንም የማነጽ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። ይኽ የሚኾነው ደግሞ መሠረታዊ የወንጅል ሕግ ላይ የተቀመጡ የማይነኩ መርኾዎችን ባልጣሰ መንገድ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማትን በሕግ እውቅና በመሥጠት ፍትሕን ማረጋገጥ ሲቻል መኾኑን ገልጸዋል።

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች የሚሠሩት ሥራ ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ምክትል ኀላፊው በመንግሥት የአሠራር ሥነ ሥርዓት ተዘጋጅቶላቸው እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ሲሠራባቸው አልነበረም። ተቋማቱን በውይይቶች ላይ ከማሳተፍ ባለፈ በተፈለገው መንገድ ድጋፍ ሲደረግላቸው እንዳልነበርም ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡትን ሥርዓት አልበኝነት፣ አለመከባበር፣ የግጭት መባባስ አንዱ ምክንያት እንደኾነ ያነሳሉ፡፡

እነዚህ የማኅበረሰብ መሠረት ያላቸው ተቋማት ይበልጥ ተጠናክረው ፍትሕን የማረጋገጥ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ነግረውናል። ጉዳዩን ከመንግሥት ባለፈ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ጭምር ትኩረት እንዲሠጡት መደረጉንም ነግረውናል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉን የእንስሳት ሃብት ልማት ለማዘመን 24 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በትኩረት እያመረቱ ነው” እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት
Next article“የሥማርት ፕሮጀክት ሲተገበር ባሕር ዳር ለነዋሪዎቿ ምቹ እና በዓለም ታዋቂ የጎብኝዎች መዳረሻ ከተማ ትኾናለች” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው