
ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በክረምቱ ወቅት ከተዘሩ አዝዕርት እና ተከልለው ከቆዩ የግጦሽ መሬቶች ላይ የእንስሳት መኖ ለማዘጋጀት የሚያስችል ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በዚህ ሥራም በቀጣይ በዓመቱ ለሚሠሩ የእንስሳት ሃብት ልማት ሥራዎች በቂ ግብዓት የሚሰበሰብበት ስለኾነ ይህን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ናቸው እየተከናዎኑ የሚገኙት፡፡ በተለይም በክልሉ ለመኖ የሚያገለግል ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰበው የግጦሽ መሬት በመኾኑ ይህን ለማሻሻል ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውም ተገልጿል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ታደሰ ንጋቱ እና አርሶ አደር አለሚቱ አታለል ሰፊ የእንስሳት ሃብት እንዳላቸው እና ይህን ታሳቢ ያደረገ የመኖ ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ የመኖ ግብዓትን በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው እንደሌሎች ሰብሎች ሁሉ በጥንቃቄ ማልማታቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የእንስሳት ልማት ሥራን እንደሌሎቹ የግብርና ሥራ ሲቆጥሩት እና ትኩረት ሲያደርጉበት አለመቆየታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ግን ከእንስሳት የሚገኘውን ገቢ እና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን ጥቅም በመገንዘብ እንደሌሎች የግብርና ሥራዎች ሁሉ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደኾነ ነው ያረጋገጡት፡፡
በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የመኖ ልማት እና አጠቃቀም ባለሙያ አበበ ምትኬ 482 ሺህ 911 ሄክታር የግጦሽ መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የግጦሽ መሬቱን አረም በማረም እንዲሁም ዩሪያ ማዳበሪያ፣ ፍግ እና ብስባሽ በመጨመር ማልማት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የግጦሽ መሬትን ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ መኖን ለማልማት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የተሻሻሉ የመኖ ልማት ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ባለሙያው ተናግረዋል። ኃይል ሰጪ እና የገንቢነት ይዘት ያላቸውን የመኖ ዝርያዎች በማልማት ለወተት ልማት፣ ለማድለብ ሥራ እና ለሌሎችም አገልግሎት የሚሠጡ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ብዙም አለመሠራቱን አስታውሰው በዚህ ዓመት ግን በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ነው ያረጋገጡት፡፡
በሰብል ስር፣ በማሳ ድንበር፣ በግል የግጦሽ መሬት ላይ፣ በእርከን ላይ፣ በጓሮ፣ በተራራ እና በቦረቦር አካባቢ ላይ በአጠቃላይ 239 ሺህ 620 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ድብልቅ መኖ መዘጋጀቱንም ባለሙያው አብራርተዋል። የሰብል ልማት ተረፈ ምርትን ለመኖ ለማዋልም በበጋው ወቅት በሰፊው ለመሥራት መታቀዱን አንስተዋል፡፡
አቶ አበበ በዘልማድ ከሚዘጋጀው መኖ በተጨማሪ በኢንዱስትሪ የሚዘጋጁ መኖዎችን መጠቀም ለላቀ ውጤት እንደሚያበቃ ተናግረዋል። ስለዚህ አርብቶ አደሩ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን አሠራር በማዘመን እና የፋብሪካ ውጤት የኾኑ መኖዎችን በስፋት በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማምጣት መጣር አለበት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ባለሙያው “የክልሉን የእንስሳት ልማት ለማዘመን 24 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በትኩረት እያመረቱ ነው” ብለዋል። እነዚህ ፋብሪካዎች በስፋት እንዲሠሩ በማድረግ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ወደ 6 ሺህ 977 ቶን የእንስሳት ምጥን መኖ ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!