የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ አሠራርን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጠ፡፡

124

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወስደው ያለፉ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ አሠራርን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የዩኒቨርስቲ ምደባ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወስደው ያለፉ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ አሠራርን አስመልክቶ የተሰጠ ማብራሪያ
የተማሪ ምደባ መስፈርቶች፡-

1. አንድ ሺህ ለሚኾኑ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፡- የምደባ ሥርዓቱ በተፈጥሮም ኾነ በማኅበራዊ ሳይንስ መስኮች አንድ ሺህ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲ እና የትምህርት መስክ ምርጫቸው ምደባ የሚካሄድ ይኾናል።

2. ውጤት:- የምደባ ሥርዓቱ እያንዳንዱ ተማሪ ያስመዘገበውን አጠቃላይ ውጤት በምደባ ሥርዓት ሂደት ውስጥ መለያ አድርጎ ይጠቀማል፡፡ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሌሎች ተፈጻሚ የሚኾኑ ሕግና ደንቦችን ባልጣሰ መልኩ ምርጫቸውን በመጠበቅ ረገድ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡

3. የዩኒቨርሲቲ ምርጫ:- የምደባ ሥርዓቱ በተማሪዎች የተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን የቅበላ አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ተማሪዎች 46 ዩኒቨርሲቲዎች ለምርጫ ቀርበውላቸዋል፡፡ መረጃው የተሰበሰበው https://portal.etherenet.edu.et ላይ ነው፡፡

4. በተማሪዎች የተመረጡ ተቋማት ያላቸው የትምህርት ፕሮግራሞች ፡- የምደባ ሥርዓቱ በተማሪዎች የተመረጡ የትምህርት ፕሮግራሞች እና የተመረጡት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን የትምህርት ፕሮግራም መሰረት ያደረገ እንዲኾን ተደርጓል፡፡
5. ጾታ ፡- በተቋማት የጾታ ተዋጽኦን ለመጠበቅ በሚኖረው የምደባ ሥርዓት የጾታ ተዋጽኦና ሚዛን እንዲጠበቅ ተደርጓል፣

6. የትምህርት ቤት ተዋጽኦ ፡- የምደባ ሥርዓቱ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚመደቡ ተማሪዎችን ተዋጽኦ በጠበቀ መልኩ እንዲኾን ያግዛል፡፡ይህም ከአንድ ትምህርት ቤት የወጡ ተማሪዎች በአንድ ዩኒቨርሲቲ ወይም ፕሮግራም ውስጥ እንዳይታጨቁ ይደርጋል፡፡

7. የውጤት ተዋጽኦ ፡-የምደባ ሥርዓቱ ተማሪዎች ያስመዘገቡትን ውጤት ታሳቢ ያረገ ሲኾን ይህም ተመሳሳይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች አንድ ላይ እንዳይመደቡ በማድረግ የተለያየ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን ቀላቅሎ ለማስተማር ያግዛል፡፡

8. ወሊድን በተመለከተ፡- የምደባ ሥርዓቱ እንደ ወሊድ ያሉ ልዩ ሁኔታዎችን ያማከለ ነው፡፡ በመኾኑም በመሰል ኹኔታ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠል የሚቸገሩ ከኾነ ትክክለኛ ለውጥና ድጋፍ የሚደረግ ይኾናል፡፡ መረጃዎቹ የተሰበሰቡት https//student.ethernet.edu.et ላይ ነው፡፡

•አስፈላጊ ማስረጃዎች: – ከትምህርት ቤታቸው የድጋፍ ደብዳቤ እና የሕጻናት የክትባት ካርድ

9. ትክክለኛ የሕክምና ቦርድ ማስረጃዎች፡- በምደባ ወቅት የጤና ችግር ኖሮባቸው ትክክለኛ የሕክምና ማስረጃ ላላቸው ተማሪዎች ምደባው በተለየ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡

• አስፈላጊ ማስረጃዎች፡- ከትምህርት ቤታቸው የድጋፍ ደብዳቤ እና ከህዝብ ጤና ተቋማት የሕክምና ምስክር ወረቀት በሦስት ዶክተሮች እና በሕክምና ዳይሬክተሩ የጸደቀ።

• የዚህ አይነት መረጃ የተሰበሰበው https://student.ethernet.edu.et በመጠቀም ነው።

10. ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መንትዮች (identical twins) ፡- በተማሪዎቹ መካከል ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መንትዮች ካሉ የምደባ ሥርዓቱ ከፍተኛ ነጥብ ያገኘው/ችው ተማሪ ከተመደበበት/ችበት የትምህርት ተቋም ቀሪው መንትያ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በቀጥታ ይመደባል። የዚህ አይነት መረጃ የተሰበሰበው https://student.ethernet.edu.et ላይ ነው።

• አስፈላጊ ማስረጃዎች፡- ከትምህርት ቤታቸው የድጋፍ ደብዳቤ እና የልደት የምስክር ወረቀት፣

11. የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች:- የምደባ ሥርዓቱ የአካል ጉዳት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች እኩል እድሎችን የሚሰጥ ሲኾን ልዩ ፍላጎቶቻቸውን እና ለምደባ መስፈርቶቻቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚሠራ ይኾናል። የዚህ አይነት መረጃ የተሰበሰበው https://student.ethernet.edu.et በመጠቀም ነው።

• አስፈላጊ ማስረጃዎች፡ ከትምህርት ቤታቸው የድጋፍ ደብዳቤ እና የአካል ችግር ያለበትን የሰውነት ክፍል የሚያሳይ ፎቶግራፍ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፣
ማሳሰቢያ:- ሀሰተኛ የሕክምና ማስረጃ የሚያቀርብ ተማሪ ያለምንም ቅድመ ሁኹታ ከምደባ ውጭ የሚኾን መኾኑን እንገልጻለን፡፡

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምክክር ሀገር ጠንካራ ነው”
Next article“የክልሉን የእንስሳት ሃብት ልማት ለማዘመን 24 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በትኩረት እያመረቱ ነው” እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት