“የምክክር ሀገር ጠንካራ ነው”

54

ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተመካከሩ ይስማማሉ፣ የተስማሙ በፍቅር ይኖራሉ፣ በፍቅር የኖሩ ሀገርን ሰላም ያደርጋሉ። አበው ከምክክር የገዘፈ ችግር የለም ይላሉ። እድሜ ለሽምግልና እንጂ ሁሉም በዛፍ ሥር አበው መክረውበት፣ የከረረውን አላልተውት፣ የሻከረውን አለዝበውት፣ ለደም የሚፈላለገውን በፍቅር አጣምረውት እርቅ ያወርዳሉ። ለግድያ የሚፈላለጉትን በፍቅር ያስተቃቅፋሉ።

እየተመካከሩ የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ ይፈታሉ፣ እየተመካከሩ የነገ መንገዳቸውን ያሳምራሉ፣ ጠንካራ ሀገር ይፈጥራሉ፣ ጠንካራ ሀገርም ለልጅ ልጅ ያስተላልፋሉ። በምክክር ደም ይደርቃል፣ በምክክር እርቅ ይወርዳል፣ በምክክር የተናወጠች ምድር ሰላም ትኾናለች።

ሀገር በምክክር ትጸናለች፣ በምክክር ችግሮቿን ትፈታለች፣ በምክክር አንድነቷን ታጸናለች፣ በምክክር ሰላሟን ታስከብራለች። ምክክር ልብ ለልብ ያገናኛል፣ የተራራቁትን ያቀራርባል፣ የተጋጩትን ያስታርቃል። ቀርቦ መነጋገር እና መወያየት ሲቻል አንደኛው የሌላኛውን ችግርና ጥያቄ ያውቃል፣ መከፋቱንም ይረዳል። ካልተመካከሩት ችግር አይፈታም፣ ሰላም አይመጣም፣ ፍቅር አይደረጅም።

ኢትዮጵያ የከበሩ እሴቶች አሏት። በእሴቶቿ ግጭቶችን እያቆመች፣ ሰላሟን እያጸናች ዘመናትን ተሻግራለች። የጠበቀ ሀገራዊ አንድነት መሥርታ በነፃነት ኖራለች። በገነባችው አንድነት ፣ አትንኩኝ ባይነት፣ የሀገር ፍቅርና የሠንደቅ ክብር በድል አድራጊነት ዘልቃለች።

ለዘመናት በዘለቀው ታሪኳ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን አዳብራለች። በጠንካራ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሕዝብ ሥነ ልቡና ቀርፃለች፣ አንድነትንም አጽንታ ኖራለች።

ኢትዮጵያዊያን በስምምነት በሚፈጥሯቸው ሕጎች፣ ደንቦችና ጠንካራ እሴቶች በፍቅር መኖርን አዳብረዋል። በየዘመናቱ የገጠሟቸውን ችግሮቻቸውን ሲፈቱ ኖረዋል። አሁንም ባልነጠፉትና በማይነጥፉት እሴቶቻቸው ችግሮቻቸውን የመፍታት ልምዶቻቸውን አልተውም። በኢትዮጵያ ከዓመታት ወዲህ የሚፈጠሩ ችግሮችን፣ ደም አፋሳሽ ቁርሾዎችን ለመፍታት ከሁሉ አስቀድሞ በቀደሙት እሴቶች አማካኝነት እንዲፈቱ ይመከራል። ምክንያቱም በቆዩት ማኅበራዊ እሴቶቻቸው አማካኝነት አይፈቱም የተባሉ ችግሮችን ሲፈቱ ኖረዋልና።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት (ፎክሎር) መምህር ብርሃኑ ቦጋለ እሴቶች አንድ ማኅበረሰብ ዋጋ የሚሰጣቸው የእኔ ብሎ የሚይዛቸው መኾናቸውን ይናገራሉ፣ አንድ ማኅበረሰብ በእሴቶች አማካኝነት መልካም ነገሮችን ያበረታታል ፣ መጥፎ ነገሮችን ያወግዛል ይላሉ።

ሰላምን መጠበቅ፣ ደኅንነት፣ መቻቻል፣ አብሮ መኖር በማኅበረሰቡ ዘንድ የተወደዱና የሚጠናከሩ ናቸው። አንድ ማኅበረሰብ በእሴቶች አማካኝነት ጠቃሚ የኾኑትን ያበረታታል፣ ጠቃሚ ያልኾኑትን ያወግዛል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ምስጢር ጠባቂነት እንዲኖር የሚያደርጉ እሴቶች አሏቸው። ማኅበራዊ እሴቶች በጋራ የተፈጠሩ፣ በጋራ የሚያኖሩ ናቸው። አንድነት ፣ ጽናት፣ ሰላምን ለማጽናት ማኅበራዊ እሴቶች ትልቅ መሳሪያዎች ናቸው፣ ሰላም የሌለው ሀገር እንደ ሀገር አይቆጠርም፣ ሰላምን ለማምጣት ደግሞ ማኅበረሰቡ በእሴቶቹ አማካኝነት ይሠራል ይላሉ። በእሴቶች አማካኝነት ልብን ይገዛሉ፣ ልብን ገዝተውም በሰላም ያኖራሉ ነው የሚሉት። ልብ በመልካም ነገር ከተገዛ፣ በአንድነት ለመኖር አያስቸግርምና።

በማኅበረሰብ ዘንድ ሰላም ቀዳሚው ነው፣ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም፣ ለሁሉም መነሻ ሰላም ነውም ይላሉ። ሰላምን ለማፅናት ማኅበራዊ እሴቶችን መጠቀም እና በጋራ መሥራትም ይገባል ነው ያሉት።

ለሀገር እና ለሕዝብ የማይጠቅሙ አካሄዶችን ማኅበረሰቡ ይነቅፋል፣ የሚነቀፉ ነገሮችን በእሴቶች አማካኝነት መከላከል ይገባልም ይላሉ። ማኅበረሰብ ሥራን ያበረታታል፣ ሀገርን የሚለውጠው መሥራት ነው፣ ሰው እስካለ ድረስ መሥራት ይገባዋል፣ ሁልጊዜም መሥራት ከተቻለ ሀገር ያድጋል ሰላምም ይመጣል።

በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተፃፉ እና ያልተፃፉ ሕጎች አሉ፣ ሁለቱም ሕጎች ማኅበረሰቡን በአንድነት ያኖራሉ፣ ማኅበራዊ እሴቶች ያስተምራሉ፣ ያዝናናሉ፣ ያጠናክራሉ፣ መልካም ነገርን ይተክላሉ፣ መጥፎ ነገሮችን ይቃወማሉ፣ ያስጠነቅቃሉ ነው የሚሏቸው።

ማኅበራዊ እሴቶች ግጭትን ይቃወማሉ ነው የሚሉት። ያለ ጥቅም የተፈጠረ የሰውነት ክፍል እንደሌለ ሁሉ ያለ ጥቅም የተፈጠሩ ማኅበራዊ እሴቶች አለመኖራቸውንም መምህሩ ይገልፃሉ።

የምክክር ሀገር ጠንካራ ነውም ይላሉ፣ ምክክር ሀገርን ያጠናክራል፣ በምክክር ሁሉም ይፈታልና። ጎረቤት ሰላም ካደረ አንተም ሰላም ታድራለህ፣ ሰላም የሚያምረው ከጎረቤት ጋር ነው። የነገር ጠማማ በሽማግሌ ይታረቃል ይላሉ። “ሽማግሌ የተቀደደ ሰማይ ይሰፋል” እንደተባለ ሁሉ በሽማግሌ የተበደለ ተክሶ፣ የበደለ ክሶ እርቅ ይኾናል፣ በመካከል የነበረው የጥል ግድግዳ ይናዳል።

የሀገርን ባሕል እሴት ማጥናት፣ መጠበቅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተማር ይገባልም ይላሉ። ሀገር በቀል እውቀት ላይ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። አሁን ላይ እሴቶችን የሚጎዱ አስተሳሰቦች እንዳሉም አንስተዋል መምህሩ።

በኢትዮጵያ አውዳሚነት የተጠናወተው አስተሳሰብ እያቆጠቆጠ፣ ግላዊነት እየተስፋፋ መጥቷልም ይላሉ። አንድን ማኅበረሰብ በሥርዓት ለመምራት ባሕሉን፣ ታሪኩን፣ ሃይማኖቱ እና እሴቱን ማወቅ ያስፈልጋል ነው የሚሉት። አንዱን ነጥሎ አንዱን መደገፍም አለ፣ የራስን ባሕልና ማንነት ማጽናት ግድ ይላልም ይላሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ብቻ የሚደግሱ የውጭና የውስጥ ኃይሎች አሉ፣ በተለይም ኢትዮጵያ በታሪክ ድል የመታቻቸው የውጭ ኃይሎች ዋና ማሸነፊያ መንገድ አድርገው የያዙት፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በአካባቢ ማከፋፈልን መኾኑን መምህሩ አንስተዋል።

በዓድዋ ድል ምክንያት በርካታ የክፋትና የመከፋፈል ሥራዎችን ያለ ማቋረጥ እንደሚሠሩም አንስተዋል። ኢትዮጵያን ለማዳከም ሃይማኖትን እና ብሔርን ነጥለው እንደሚያጋጩ ነው ያመላከቱት። ከውጭ የሚመጡ ሴራዎች አሁን ሀገር ላለችበት ሁኔታ መነሻ ናቸውም ይላሉ።

የብዙኀን መገናኛ ተቋማት ማኅበራዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ሰላም እንዲጸና መሥራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል። ሕግ እንዲከበር ማድረግ፣ ሕግን ማክበር እና ማስከበር ይገባል፣ ሕግን የማያከብር ትውልድ ዘመናዊ አይደለምና።

በእጅ የያዙት ወርቅ እንዲሉ ማኅበራዊ እሴቶችን በሚገባ አልተጠቀምንባቸውም። የእናት ጥቅም የሚታወቀው ስትታጣ ነው፣ ጥቅሙን ሳያጡ ማወቅ ግድ ይላል ብለዋል። የራስን አለመናቅ የተገባ ነው፣ በመነጋገር፣ በውይይት ሀገርን ማቆም ይገባል ነው ያሉት።

ሁልጊዜ መመካከር መፍትሔ ያመጣል ፣ አንድነትን ያደረጃል፣ ፍቅርን ያሰፋል፣ ግጭትን ያስቀራል፣ ሀገርን ያጠነክራል፣ በምድሯና በሕዝቦቿ ዘንድ ሰላም ይኾናል።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ ክልል ያጋጠመውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next articleየተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ አሠራርን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጠ፡፡