“በዓሉ ብዝኃነትን፣ መቻቻልን እና አብሮነትን በማጎልበት ዴሞክራሲ እና ዘላቂ ሰላምን የምናጠናክርበት ይኾናል” ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ

63

ባሕር ዳር:ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም(አሚኮ)የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለውን ሚና በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለልጸዋል።

በሶማሌ ክልል አዘጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል።

ሕገ መንግሥቱ እና ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ አስተምህሮን በአግባቡ ተደራሽ ባደረገ መልኩ ለማክበር የአሠልጣኞች ሥልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በዓሉ ቀኑን ከማሰብ ባለፈ ሕገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን የሚታደስበት ነው።

ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለው በማረጋገጥ ጭምር እንደሚኾን ተናግረዋል።

ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ለሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነት እና አንድነት ዋስትና የሰጠ መኾኑን ያስታወሱት ወይዘሮ ዛህራ “በዓሉ ብዝኃነትን፣ መቻቻልን እና አብሮነትን በማጎልበት ዴሞክራሲ እና ዘላቂ ሰላምን የምናጠናክርበት ነው” ብለዋል።

“ለዘመናት አስተሳስረውን የኖሩት እሴቶቻችን የሀገራችንን አንድነት ማፅናት ችለዋል” ያሉት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ፣ በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባሕል እና እሴቶች ለማጎልበት ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል።

ሥልጠናው በዓሉን ምክንያት በማድረግ በቀጣይ በፌዴራሊዝም እና ሕገ-መንግሥታዊ አስተምህሮ ላይ አካታች መድረኮች እና ውይይቶች ለማዘጋጀት ያለመ መኾኑን ጠቁመዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኑኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነት እና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንችይርጋ መለሰ ሕብረ-ብሔራዊ እንድነት እና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በትኩረት እየተሠራ ነው።

በብዝኃነት መካከል እኩልነት፣ አንድነት፣ ዴሞክራሲ እና ሰላምን ለማፅናት ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መኾኑን ጠቁመዋል።

“በዓሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት በመኾኑ ሀገራዊ እንድነትን ይበልጥ ለማጎልበት ሚናው የጎላ ነው” ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ከሁሉም ክልል እና ሁለቱ የከተማ አሥተዳደሮች የመጡ ምክትል አፈ-ጉባኤዎች ተሳታፊ መኾናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፌዴራል ሥርዓቱ አዎንታዊ አበርክቶ ባላቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አደረጃጀቶች የሚሳተፉባቸው መድረኮች እንደሚካሄዱም ጠቅሰዋል።

በበዓሉ የፌዴራል ሥርዓቱ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ እና ብዝሃነት እንደፀጋ በመቀበል የሚኖረውን ፋይዳ ለማስገንዘብ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠው የሕዝቦች ነፃነት ፤ ለሀገራዊ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም መሠረት መኾኑን አፅንኦት የሚሰጥበት እንደኾነ ተናግረዋል።

18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ሕዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር ይታወቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሕራ” በአማራ ክልል በዘላቂ ሰላም እና ግጭት አፈታት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችለውን መርሐ ግብር ይፋ አደረገ።
Next articleየቅጥር ማስታወቂያ