
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አዲስ ሕይወት ሪሃብሊቴሽን እና ሪኢንተግሬሽን አሶሴሽን (አሕራ) በክልሉ በቀጣይ አራት ወራት በዘላቂ ሰላምና ግጭት አፈታት ላይ ለመሥራት የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል።
የድርጅቱ አስተባባሪ አሕመድ ሙሐመድ እንደገለጹት ድርጅቱ በቀጣይ በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የማኅበረሰብ ተወካዮችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችን እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
ማኅብረተሰቡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት እና በሽግግር ፍትህ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የአቅም ግንባታ እና የውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻችም ገልጸዋል።
በክልሉ የተሻሉ የግጭት አፈታት ተሞክሮዎችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋትም በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ አሕራ ትልቅ አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል። በዘላቂ ሰላም ግንባታ እና በግጭት አፈታት ላይ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ በመሥራት የፍትሕ ተቋማትን አጋዥ ኾኖ እየሠራ መኾኑን ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት።
ያለ ማኅበረሰቡ ተሳትፎ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይቻል ያነሱት ኀላፊው የክልሉን ሰላም ለማስፈን ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
አሕራ ለ20 ዓመታት ያህል የሠራ ሲኾን መሰረቱን በአማራ ክልል በማድረግ ነበር ሥራውን የጀመረው። በተለይም ደግሞ በክልሉ በዘላቂ ሰላም፣ በሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት፣ በሰብዓዊ መብት፣ በሴት ልጅ ግርዛትና የሴት ልጅ ጥቃት እንዲኹም ታራሚዎች መብታቸው እንዲጠበቅና ግዴታቸውንም እንዲወጡ ማድረግ ላይ ሲሠራ ቆይቷል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!