“ሀገር ከሚወድቅብህ፣ ተራራ ይውደቅብህ”

82

ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሀገሬው ሰው “እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣ ሀገር የሞተ እንደው ወዴት ይደረሳል” እያለ ይቀኛል። ሀገር ከሁሉም የላቀች፣ ከሁሉም የበለጠች መኾኗን ሲያስረዳ።

ሀገር ካለች ሁሉም ይኖራል ፤ ሀገር ከሌለች እንኳን ኑሮው ሞትም አያምርም። ወልዶ ለመዳር፣ ድሮ ለመኳል ሀገር ታስፈልጋለች። ሀገር ከሌለች የትም አይደረስም፣ የትም አይደገስም፣ የትም አይለቀስም። የሰው ሀገር ሀገር አይኾንምና።

ሀገር ሁሉንም ናት፣ ሀገር ለሁሉም ናት ፣ ሀገር የሁሉም ናት። ሀገር እትብት ናት ከአንጀት ጋር የሚያያይዟት፣ ሀገር ትዝታ ናት ሁልጊዜም የማይረሷት፣ ሀገር ስም ናት የሚጠሩባት፣ ሀገር ጌጥ ናት የሚያጌጡባት፣ ሀገር ማንነት ናት የሚገለጡባት፣ ሀገር ቅኔ ናት የሚቀኙላት፣ ሀገር ቃል ኪዳን ናት የሚያከብሯት፣ ሀገር ክብር ናት የሚከበሩባት፣ ሀገር ከሁሉም በላይ ናት ስጋና፣ ደምን ክቡር ሕይወትን የሚሰጧት፣ ሀገር ከምንም በላይ ናት ሁሉንም የሚሰጧት።

አበውና እመው ሀገርን በደምና በአጥንታቸው አጸኗት፣ ጠበቋት፣ አጽንተውም አስረከቧት። የቀደሙት አባቶችና እናቶች የሀገር ፍቅር የሚያጸኑባቸው፣ አንድነትን የሚያጠናክሩባቸው፣ ጠብና ጥላቻን የሚገድሉባቸው፣ ሰላምን የሚሰብኩባቸው፣ መተባበርን የሚያበረታቱባቸው፣ ጽናትን፣ ጠንካራ ሠራተኝነትን የሚያሳዩባቸው፣ ስንፍናን የሚወቅሱባቸው፣ ሌብነትን የሚያወግዙባቸው፣ መሥጠትን የሚያሞግሱባቸው እሴቶች አሏቸው። በእሴት ትውልድን ከትውልድ ጋር አገናኝተዋል። በእሴት አንድነትን አጠንክረው ሀገርን አሻግረዋል።

እሴቶች ሀገር በአንድነቷ እንድትቀጥል፣ ሰው ከሰው ጋር እንዳይነጣጠል ማሰሪያ ገመዶች ናቸው። ጠንካራ እሴቶች ሲከበሩ ጠንካራ ሀገር፣ ጠንካራ አንድነት ይኖራል። እሴት ሲሸበር የሀገር አንድነት ይሸረሸራል፣ የሀገር ፍቅር ይቀዘቅዛል፣ ሰላምና ፍቅር ይጠፋል። ኢትዮጵያውያን በልብ ላይ በጻፏቸው ሕጎቻቸው አማካኝነት ጥልን እየገደሉ፣ ፍቅር እያደላደሉ ለዘመናት ኖረዋል። አይታለፍም የተባለውንም አልፈዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እሴቶችን አለመጠቀም እና ለእነርሱ ክብር ካለመስጠት የመጡ እንደኾነ ይነገራል። ለዘመናት ኢትዮጵያዊያንን አስተሳስረው የቆዩ አሴቶችን መጠቀም ደግሞ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፉ ጉዳይ ነው።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) ማኅበራዊ እሴቶች አንድ ማኅበረሰብ በሰላም ፣በመግባባት እንዲኖር በውስጣቸው አስገዳጅ ሕግ ያላቸው ጉዳዮች ናቸው ይሏቸዋል። የማኅበራዊ እሴቶች ራሳቸውን የቻሉ ሕግና ደንብ አላቸው፣ ሕግና ደንባቸውም በማኅበረሰቡ የወጡ፣ ማኅበረሰቡም የሚገዛባቸው ናቸው። ማኅበራዊ እሴቶች በሕግ የተመሉ መኾናቸውንም ያነሳሉ። ሕግ ያላቸው በመኾናቸው ደግሞ ሕዝብ እንዲገዛላቸው ያደርጋሉ፣ ሕጎችን የሚጥስ ካለ በእሴቶች አማካኝነት ይቀጣል ፣የማኅበራዊ እሴቶች ለዘመናት ሕዝብን በአንድነት እና በሰላም ያኖሩም ናቸው።

ሰው ከሰው ጋር ተስማምቶ ፣ አንዱ የተቀበለውን ሌላው ተቀብሎ መኖር ካለ ጥሩ ማኅበራዊ እሴት አለ። ማኅበረሰብ ተስማምቶ በፈጠራቸው እሴቶች አማካኝነት አንድነትን ያጠናክራል ፣ የጋራ ሰላምም በጋራ ያውጃል። በእሴቶች አማካኝነት ያፈነገጠን ወደ ማኅበሩ ይሰበስባል፣ የጋራ ማኅበራዊ እሴት ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቀለም አይለይም፣ ሁሉንም በአንድነት በሰላም ያኖራል እንጂ።

ጠንካራ ማኅበራዊ እሴት ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያለያይ ነገር አይኖርም፣ ልዩነትን አጣጥሞ የመኖር ልምዱ ከፍያለ ነው ይላሉ የባሕል ጥናት መምህሩ። በጠንካራ ማኅበራዊ እሴት አማካኝነት የተጣላ ሲኖር ማስታረቅ ፣ያዘነን ማጽናናት፣ ሰላም እንዲኖር ማድረግ ይኖራል። በማኅበራዊ እሴቶች የሚሰበከው አንድነት ፣ ሰላምና ፍቅር ነው። ይህ አይነት መልካምና የዳበረ እሴት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ይዘውት የቆዩት ነው። ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖተኞች ናቸው፣ ሃይማኖቶቻቸው ደግሞ ፍቅርን ሰላምንና አንድነትን ይሰብካሉ።

ማኅበራዊ እሴቶች ሰበዓዊነትን ይሰብካሉ፣ ሰበዓዊነት ሲቀድም አንድ ሰው በሰላም እንዲኖር ያደርጋል። የማኅበራዊ እሴቶች ዓላማ ሰውን በሰላም ማኖር ነው፣ አንድን ሕዝብ በብዛት የሚያስተዳድረው ከረጅም ዘመናት ጀምሮ የፈጠረው እሴት መኾኑንም ይገልፃሉ።

ማኅበራዊ እሴቶች የሚያሸንፉት ልብን ነው ፣ የአንድን ማኅበረሰብ ልብ የሚያሸንፉትና በሰላም የሚያስገዙት ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው። አንድን ማኅበረሰብ ማሳመን የሚቻለው በሚያምንባቸው እሴቶች መሄድ ሲቻል ነው ፤ ጦርነት ጉልበትን ያሸንፋል ፤ እሴት ግን ልብን ያሸንፋል ፤ የሚያሸንፈውም በፍቅር ፣በሰላምና በአንድነት ነው በግድ አይደለም ፤ አምኖበት እንዲሸነፍ ያደርገዋልና ነው የሚሉት የባሕል ጥናት መምህሩ።

ማኅበረሰብ ለዘመናት ያቆያቸው የሽምግልና ሥርዓቶች ግጭትን ያስቆማሉ፣ ፍቅርን ያነግሳሉ፣ ሰላምን ያጸናሉ፣ ከጉልበት ይልቅ እሴት የሕዝብን ልብ ይገዛል፣ አሳምኖም ያስገዛል። የቆዩ የሽምግልና ሥርዓቶች ደም ያደርቃሉ፣ ለግድያ የሚፈላለጉትን ያስታርቃሉ፣ እነዚህ እሴቶች ማኀበረሰቡ በሰላም እንዲኖር ያላቸው ፋይዳ ላቅ ያለ ነው፣ ማኅበረሰቡ ሰላሙን የሚጠብቅባቸው ብርቱ እሴቶች አሉት። ማኅበረሰቡ ለሰላም ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ሰላምን ከሰው ልጆች ብቻ ሳይኾን ከእንስሳትና ከተፈጥሮ ጋርም ይፈልጋል ነው ያሉን።

ማኅበረሰብ ለሰላም ካለው ትልቅ ግምትና ጥንቃቄ የተነሳ እንኳን ሰው እንስሳት በግፍ ሲገደድ ሲያይ ይቀጣል፣ ይገስጻል ነው የሚሉት። አንድ ሰው መጥፎ ነገር እንዳያደርግ የሚያደርጉ ጥብቅ እሴቶች መኖራቸውንም አንስተዋል። ማኅበረሰብ የማይጠቅሙትን ነገሮች አይሠራም ፤ የሚሠራቸው እሴቶች አንድነቱን የሚያስጠብቁለትን፣ ሰላም የሚያመጡለትን በፍቅር የሚያኖሩትን ነው። ማኅበራዊ እሴቶች ታሪክ መንገሪያ ፣ ታሪክ ማቆያ ፣ ሰላምን ማጽኛ ፣ ፍቅርና አንድነትን ማጎልበቻ ናቸው ፤ የቀደመውም ማኅበራዊ አንደነት እንዳይናጋ የሚያደርግባቸው ናቸው ይሏቸዋል።

ማኅበራዊ እሴቶች ተከታዩን ትውልድ የመግራት ፣ የማሠልጠንና ወደ ፊት በሰላም እንዲኖር የማድረግ ዓላማ እንዳላቸውም ያነሳሉ። በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሽማግሌ ያለውን ማክበር ግድ ይላል ፤ ሽማግሌዎች በሀገር ይወከላሉ ፤ ሀገርም በጠየቀች ጊዜ እምቢ አትባልም። ሽማግሌዎች በሚያስታርቁ ጊዜ እምቢ ያለን ሰው ሀገር ከሚጫንህ እና ተራራ ከሚጫንህ የትኛው ይሻልሃል ይሉታል፣ ተራራ ቢወድቅብህ ሀገርህ ያነሳልሃል፣ ሀገርህ ቢወድቅብ ግን ማን ያነሳልሃል ይሉታል።

ሀገር ማለት ሽማግሌዎች ናቸው። ይህ አባባላቸው እሴት ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ነው። እምቢ ያለውም እሺ ብሎ ይታረቃል። እምቢ ቢል ግን ከሀገር ይወጣል። ከሀገር ወጣ ማለት ከማኅበረሰቡ ተገለለ ማለት ነው ይላሉ። ማኅበራዊ እሴት ለአብሮነት የማይተካ ሚና አላቸው።

መምህሩ ስለ እሴቶች ሲናገሩ ዘመናዊነት በሚል እሳቤ ዘመናዊነትን በተዛባ መንገድ መተርጎም እሴትን ጎድቶታል። አሁን ላይ እያገለገለህ ያለ እሴት ካለ እድሜው ረጅም ቢኾንም ዘመናዊ ነው ፤ ምክንያቱም ዘመኑን ዋጅቷል። ብዙ ጊዜ ዘመናዊ የሚባሉት ከውጭ የሚመጡት ፣ እኛን የማይመስሉትና የማይገልጹት ናቸው ይላሉ። ዘመናዊነት ዘመኑን የዋጀ የራስ እሴት እና ማንነት ነው። ችግር ከፈቱ ፣ አብረው ካኗኗሩ ፣ ሰላም ካመጡ ፣ ዘመኑን ከዋጁ ዘመናዊ ናቸው።

እያበበ የመጣው ወገንተኝነት አብሮ መኖርን እያሳጣ ፣ አንድነትን እያጠፋ ፣ ፍቅርን እያዘቀዘቀ ይሄዳል። አንድነት የማይፈልጉ አግላይ ማኅበረሰብን አንድ አድርገው የኖሩ የአንድነት መገለጫዎችን ያጠፋሉ ፣ ያደክማሉ ፤ በኢትዮጵያም የአንድነት መገለጫ የኾኑ እሴቶችን የሚጎዱ አካሄዶች አሉ ነው ያሉት።

ማኅበራዊ እሴትን አለመጠበቅ ለእርስ በእርስ ግጭት ዳርጓል ፤ የማኅበረሰብ ታላቁ እሴት ለቃል መታመን ነው። ቃልን አለማክበር ለግጭት ይዳርጋል ፤ በሀገር ላይ የሚታየው ግጭትም ቃልን ካለማክበር ጋር የመጡ ናቸው ይላሉ። በማኀበረሰቡ ዘንድ እጅግ የተከበሩ እሴቶችንና ተቋማትን መድፈር ለግጭት ይዳርጋል ፤ ማኅበራዊ እሴቶችን ማክበርና ማስከበር ግጭትን ያስቆማል ነው ያሉት። አስተሳሰብን መቀየር የሚቻለው በአንድ ጊዜ ሳይኾን ቀስ በቀስ መኾኑንም አንስተዋል።

እሴትን እና ማኅበራዊ ሥሪቶችን ለመጠበቅ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የማኅበራዊ ጠቅላላ ጠቀሜታ ማኅበረሰብን በሰላማዊ መንገድ ማኖር ነውም ይላሉ። የሀገርን ሕግ ከባሕልና ከእሴት መቅዳት እንደሚገባም አንስተዋል። ሀገርን ማሳደግ የሚቻለው ራስን መኾን ሲቻል ብቻ ነው። ሌላውን ኾኖ ሀገርን ማሳደግ አይቻልም ፤ የራስን ባሕል መሠረት አድርጎ የእድገት አቅጣጫን መንደፍ ይገባልም ብለዋል። የራስን መጠቀም ያሳድጋል ፤ ከፍ ከፍም ያደርጋል።

ሀገር ከሚወድቅብህ ተራራ ቢወድቅብህ ይሻላል በሚል ብሒል የአበውን ቃል መስማት፣ መስማማት፣ አንድነትን መፍጠር ፣ ችግሮችን በቆዬው እሴት መፍታት እንደሚሚገባም መምህሩ አሳስበዋል።

ስኬታማ የእድገት ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሠረታቸው ባሕልና እሴትን መጠቀም ነው። ኢትዮጵያም ለዘመናት ይዛቸው የኖረቻቸውን እሴቶች መያዝና በእነርሱ መቃኘት አለባት ነው ያሉት።

ከሁሉም ሀገርን አስቀድሞ ሀገር መሠረት ናትና፣ ሁሉንም ለሀገር ስጡ ሀገር እጥፍ አድርጋ ትመልሳለችና፣ ሁልጊዜም ሀገርን ከፍ ከፍ አድርጉ በሀገር ከፍታ ውስጥ የራስ ከፍታ አለና።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የ2023ቱን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ ታስተናግዳለች።
Next article“አሕራ” በአማራ ክልል በዘላቂ ሰላም እና ግጭት አፈታት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችለውን መርሐ ግብር ይፋ አደረገ።