ኢትዮጵያ የ2023ቱን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ ታስተናግዳለች።

58

ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እ᎐አ᎐አ የ2023ቱ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ገለጸ።

ጉባኤው በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አዘጋጅነት እ.አ.አ ከህዳር 16 እስከ 18 አዲስ አበባ በሚገኘው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ይካሄዳል።

በጉባኤው ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የተመድ አጋር አካላት እንዲሁም ቁልፍ የልማት እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በዚህም በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ ስላሉ አስቻይ ኹኔታዎችና ችግሮች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ወጣት ተመራማሪዎችና ምሁራን መፍትሔ ጠቋሚ የኾኑ የጥናት ውጤቶቻቸውን ለአስፈጻሚ አካላት እንዲያቀርቡ ዕድል እንደሚፈጠርም ተመላክቷል።

አፍሪካ እ᎐አ᎐አ በ2063 በኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ለማስመዝገብ የያዘችውን ውጥን ለማሳካት ጉባኤው የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ፤ መካሄድ ከጀመረበት እ᎐አ᎐አ ከ2006 ጀምሮ ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ማነቆ በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ጥናቶች የቀረበበት፣ ምሁራንና የሕግ አውጪዎችን ለማገናኘት ዕድል የተፈጠረበት ነው።

ኢዜአ እንደዘገበው ጉባኤው ሰፊ የዕወቀት ሽግግር እየተደረገበት መኾኑን የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታውሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉን የስንዴ ምርታማነት ለመጨመር አርሶ አደሮች ግብዓት በወቅቱ እንዲደርሳቸውና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች እንዲኖራቸው እንሠራለን” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next article“ሀገር ከሚወድቅብህ፣ ተራራ ይውደቅብህ”