
ደሴ: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከበጋ መስኖ ስንዴ ከ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው የ2016 የበጋ መስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋጨፋ ወረዳ አካሂዷል፡፡
በስንዴ ዘር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) የክልሉን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በክልሉ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር ይሸፈናል። ከዚህም ከ9 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ዶክተር ድረስ።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የስንዴ ልማት ሀገራችን በምግብ ራሷን እንድትችል እና ከልመና እንድትላቀቅ የሚያስችል ተኪ የሌለው ሥራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም የስንዴ ምርታማነትን ለመጨመር አርሶ አደሮች ግብዓት በወቅቱ እንዲደርሳቸውና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች እንዲኖራቸው ይሠራል ነው ያሉት።
የግብርና ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቅ ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!