“ሰላም እስትንፋስ ናትና ጠብቋት”

75

ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ባለች ዘመን አዝመራው ያምራል፣ አውድማው በምርት ይጨነቃል፣ ጎተራው ይሞላል፣ ገበያው ይጠግባል። የሀገሬው ሰው ሲመርቅ “ሰላም ይስጠን፣ የእለት ጉርስ የዓመት ልብስ አያሳጣን፣ ገበያው ጥጋብ ይሁን” ይላሉ።

ሰላም ሲኖር ሰርቶ መጉረስ፣ ለፍቶ መልበስ አይከብድም። ሰላም ከሌለ ግን ሰርቶ መጉረስም፣ ለፍቶ መልበስም አይቻልም። ሰላም በጠፋ ጊዜ እንደወጡ ይቀራል። ሰላም በሌለ ጊዜ መከራ ይበዛል፤ ውጣ ውረድ ይበረታል።

ሰላም እስትንፋስ ናትና ጠብቋት፣ ሰላም የመኖር መሠረት ናትና ተንከባከቧት፣ ሰላም እንደ ዐይን ብሌን ናትና አብዝታችሁ ተጨነቁላት። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተሟላ ሰላም ከጠፋ ጊዜያት ተቆጥረዋል፣ ኢትዮጵያውያን በሰላም እጦት ምክንያት ይሳቀቃሉ፣ ከአንድ ቀዬ ወደ ሌላኛው ቀዬ ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ።

በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የደሴና አካባቢው አስተባባሪ ወንጌላዊ አማረ ዓለሙ ሰላም ከምግብ በላይ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው ይላሉ።

የሰላም መነሻው አምላክ ነው የሚሉት ወንጌላዊው ሰላም አይደለም ለሰዎች ለእንስሳት ያስፍለጋል ብለውናል። እንስሳት በዱር በገደሉ፣ በዋሻ በስንጥሩ ለመኖር ሰላምን ይሻሉ፣ ያለ ሰላም በጫካም ውስጥ ለመኖር ይቸገራሉ፣ ሰላም እስትንፋሳችን ነው። ያለ ሰላም ምንም ማድረግ አይቻልም፣ ስለ ሰላም እንጸልያለን፣ ስለ ሰላም እናስተምራለን ፣ ስለ ሰላም እንመሰክራለን ነው ያሉት።

ሰላም የሚመነጨው ከራስ ነው፣ ከየትም አናመጣውም፣ አምላክ የሰጠንን መጠቀም ግድ ይላልም ይላሉ። ስለ ሰላም ከጸለይን፣ ስለ ሰላም ካስተማርን፣ ስለ ሰላም ከሠራን ሰላም ይሆናልም ብለዋል ወንጌላዊው አማረ።

ወንጌላዊው አማረ ስለ ሰላም ሲናገሩ ሰላም የመጀመሪያው የጸሎት ርእሳችን ነው ብለዋል። ሰላም ዋናው ጉዳያችን ነው፣ አማኞቹም ስለ ሰላም ይጸልያሉ፣ ስለ ለሰላም ይመክራሉ ብለዋል። ሰላምን የሰጠን አምላክ እያመለክን ስለ ሰላም እንኖራለን። ምዕመናን ትርፋቸው ፍቅር ነው፣ ተስፋቸው ሰላም ነው። ሕይወታቸውንም የሚያሳምረው ሰላም ነው ብለዋል።

ክፉም በጎም እንሥራ በአምላክ ፊት ነን፣ በአምላክ ፊት ደግሞ የተሻለ ሥራ ልንሠራ ይገባል፣ ያን ጊዜ ሰላም ይሆናል፣ አምላክም በሥራችን ደስ ይሰኛል ይላሉ። በችግሮች ምክንያት እርስ በእርስ እየተጠፋፋን ነው፣ ለክርስቲያን ሁሉ አስርቱ ትዕዛዛት ራሱን የሚያይባቸው መስታውቶች ናቸው፣ ትዕዛዛቱን ሲያከብርም ከጥልና ከጥላቻ ይርቃል። ከበቀልም ይሸሻል፣ ወደ ፍቅርና ሰላምም ይቀርባል ነው ያሉት።

ወንጌላዊ ሲናገሩ አሁን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን በንስሐ ጊዜ ላይ ያሉ ይመስሉኛል፣ የንስሐ ዘመናቸውን እየተቀበሉ ነው። ይህ ዘመን ሲያልፉ ደግሞ ኢትዮጵያ ሰላምን ታገኛለች። የሚያስደንቁ እሴቶች አሉን፣ ደም የሚደርቅባቸው፣ ቂም የሚረሳባቸው፣ በቀል የሚተውባቸው፣ እነርሱን ትቶ፣ የጥንት የጠዋቱን ረስቶ መገዳደል የተገባች አይደለችም ነው የሚሉት። አሁን ወደ ፊት የነበረው ሩጫችን አቆመን ወደ ኋላ እየሮጥን ነው፣ ወደኋላ መሮጥ አወዳደቅን ያከፋል። ነገር ግን ወደኋላ መለስ ብለን የምናያቸው እሴቶች፣ አኩሪ ታሪኮች፣ የሕንፃ ጥበቦች እና ሌሎች መልካም ጉዳዮችም አሉ ብለዋል።

አግባብ ነው ወይስ አግባብ አይደለም ብለን ሳንጠይቅ የምንሄድባቸው መንገዶች ለጦርነት አና ለውድቀት ምክንያት ኾነውናልም ነው ያሉት። ጦርነት ባነሳን ጊዜ የምንጎዳው ቤተሰቦቻችን ፣ ልጆቻችን እና ሀገራችንን ነው፣ ይህ ደግሞ ጠቃሚ ጉዳይ አይደለም ብለዋል ወንጌላዊው።

በሰላም እጦት ምክንያት ልጅ ወላጆቹን አልቀበረም፣ ወላጅም የልጆቹን ደስታ አላዩም፣ የሰላም እጦት የሚዋደዱትን አራርቋል፣ እናትና ልጅን አነፋፍቋል፣ ችግሮች ነበሩ፣ አሉ ፣ ይኖራሉ፣ መፍትሔያቸውም ሰላም ብቻ ነው። ከሰላም የተሻገረው መከራዎችን ያራዝም ይሆናል እንጂ ፍቅርን አይሰጥም።

ተመካክረው የሠሩት ሥራ ችግር አያመጣም፣ እያንዳንዱ ችግር ከውይይት አያልፍም ይላሉ። ትዕግሥት ችግሮችን ትፈታለች፣ መከራዎችንም ታሳልፋለች ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር ናት፣ አፍሪካ ተስፋ ታደርጋታለች፣ ለዓለምም ተስፋዋ ናት፣ ተስፋ ያላትን ሀገር ደግሞ በአንድነት መጠበቅ እና በሰላም መኖር የተገባ ነው ብለዋል ወንጌላዊው።

ወደራሳችን እንመለስ፣ አንድ እንሁን፣ ስንመካከር እንጂ ስንገዳደል አያምርብንም፣ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ መኖር አደጋ አለው ነው ያሉት። ሊነጋ ሲል ይጨልማል፣ ነገ ይነጋል፣ ነገ ሰላም ይሆናል፣ ዛሬ ላይ ግን ስለ ሀገር መኖር አለብን፣ በምክንያት እንኑር፣ ለሀገርና ለሕዝብ እናስብም ብለዋል። ልጆቻችንን ፍቅር እናስተምራቸው። ለነገረኞች ጀርባችን እንስጣቸው ነው ያሉት ወንጌላዊው አማረ። ሰላም ግን እስትንፋስ ናት ጠብቋት፣ ጠብቃችሁም ያለ ሰቀቀን ተንፍሷት፣ ያለ በደል ተመላለሱባት።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረተው የቆዳ ምርት ውስጥ ወደ ገበያ የሚቀርበው ግማሹ ብቻ ነዉ” የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next article“የክልሉን የስንዴ ምርታማነት ለመጨመር አርሶ አደሮች ግብዓት በወቅቱ እንዲደርሳቸውና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች እንዲኖራቸው እንሠራለን” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን