
አዲስ አበባ: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረተው የቆዳ ምርት ውስጥ ወደገበያ የሚቀርበው ግማሹ ብቻ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ገልጿል።
የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቆዳ ልማት ሥራዎች ላይ ከዘርፉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ 165 ቢሊዮን የሚደርስ የቀንድ ከብት ሃብት እንዳላት ጠቅሰዋል። የሚገኘው የቆዳና ሌጦ ሃብት በዚሁ ልክ በርካታ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
በዘርፉ ላይ ባለው ማነቆ ምክንያት የተገኘው ምርት በሙሉ ወደ ገበያ እየቀረበ አለመኾኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከሚመረተው ምርት ግማሹ ብቻ ለገበያ እየቀረበ መኾኑን ነው ያመላከቱት። ይህም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እያሳጣ ነው ብለዋል። የመጓጓዣ እጥረት፣ ምርቶች የሚቀርቡበት ሰፊ ገበያ አለመኖር እና የግብዓት አቅርቦት እጥረት ዋነኛ የዘርፉ ማነቆዎች ኾነው ተነስተዋል።
የቆዳ ምርት በየዓመቱ ከ8 በመቶ በላይ እያደገ ያለ ዘርፍ እንደኾነም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በቆዳ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መኾን ሲገባት ባለው የአሠራር ችግር ምክንያት አቅሟን መጠቀም ሳትችል ቆይታለች ነው ያሉት።
ይህን ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥናት ሲደረግበት ቆይቶ ዛሬ የጥናቱ ውጤት ለባለድርሻ አካላት ለውይይት ቀርቧል። በጥናቱ መሰረት ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ዘርፉን ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በሚያስችል መልኩ ወደ ሥራ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዛሬ ውይይት የተደረገበት የቆዳ ልማት ስትራቴጂ ከ 2016 እስከ 2025 ዓ.ም ባሉት 10 ዓመታት የሚተገበር ነው።
ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!