“የከተማዋ ነዋሪዎች መብታቸውን በልመና እና በግዥ ማግኘት የለባቸውም” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

51

ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማው በ2016 በጀት ዓመት ለማኅበራዊ ዘርፍ ልማቱ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አሳውቀዋል።

በትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት እንደሚሰጠውም አመላክተዋል።

ኅብረተሰቡንና ሌሎች አጋር አካላትን በማሳተፍ የቅድመ መደበኛና መደበኛ ትምህርትን ጥራትን ለማስጠበቅ አንድ ፕሮጀክት በቅርብ ጊዜ ይፋ እንደሚኾን ገልጸዋል።

ለዚህም የባሕር ዳር ከተማ ልማትና ዘላቂ እድገት የሚያሳስባቸው ሁሉ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ባሕር ዳር ከተማ ለስፖርታዊ ክዋኔዎች ያሏትን ተፈጥሯዊ ምቹነት በመጠቀም የስፖርት ማዕከል እንድትኾን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተናገሩት።

ሁሉንም ዓይነት የስፖርት ዘርፎች የምታስተናግድ እና የስፖርት ቱሪዝም ከተማ ለማድረግም እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች፣ ሎጂዎች እና መዝናኛዎች እንዲኖሩ እናደርጋለንም ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ የጣና ሐይቅን ውበት በመጨመር እና የከተማዋን ገጽታ በመገንባት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ እንዲኖረው እንሠራለን ነው ያሉት።

የጣና እና የዓባይ ዳር የመዝናኛ ልማት ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና በመሥህብ ቦታነት ተጨማሪ ልማቶች እንደሚኾኑ ገልጸዋል።

ባሕር ዳር ከተማ ጽዱ እንድትኾን የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ማሻሻል፤ እንዲሁም ጎርፍ ሥጋት የማይኾንባት ከተማ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚኖሩም ነው የተገለጸው።

የባሕር ዳርን አረንጓዴ ከተማነት ጠብቆ በአግባቡ በማልማት ሳቢና ማራኪ፤ በትንሽ ሥራ ትልቅ ውበት ያላት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ያመላከቱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ”በአቅማችን ልክ ሠርተን ለከተማዋ ነዋሪዎች ተጨባጭ ለውጥ እናሳያለን” ብለዋል።

በተንሰራፋው የአገልግሎት አሠጣጥ ችግር ላይ የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ ያሉበትን ክፍተቶች ለማስተካከል ቅደም ተከተል ተሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

”የከተማዋ ነዋሪዎች መብታቸውን በልመና እና በግዥ ማግኘት የለባቸውም” ሁሉም ነገር ገንዘብ ካልተከፈለ እንደማይገኝ አድርጎ የማሰቡ ልምድ መቀረፍ አለበት ብለዋል።

”እኛም የአገልግሎት ሥርዓቱን በማሻሻልና ከዚያም ያለፈውን ተጠያቂ በማድረግ እንሠራለን” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኅብረተሰቡም የተገልጋይነት መብቱን የሚያስከብር ሲኾን ችግሩ እንደሚቀረፍ አመላክተዋል።

“በዚህ በጀት ዓመትም ይህንን ችግር እንሻገረዋለን” ነው ያሉት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከጸጥታና ፍትሕ ሥራዎች አኳያ የሚታዩ ጉድለቶችን ለመቅረፍ እንሠራለን ብለዋል።

ከጸጥታ መዋቅሩ አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን በቁርጠኝነት በማረም በደል ደረሰብኝ ብሎ ሲሄድ አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድበትን እና ከፍትሕ አኳያም አጥፊዎች ተገቢ ቅጣት የሚያገኙበት አሠራር ለመፍጠር እንደሚሠራ አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሊዮኔል ሜሲ ለስምንተኛ ጊዜ የባሎን ደ’ኦር አሸናፊ ኾነ።
Next articleሉሲዎች የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ በአቡጃ ያደርጋሉ።