
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት ምሽት በፈረንሳይ ፖሪስ በተካሄደው የሽልማት መርሐ ግብር የየዘርፉ ምርጦችም ተለይተዋል። በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የተካሄደውን የ2023 የባሎን ደ’ኦር ሽልማት ባለፈው ዓመት ሀገሩ አርጀንቲን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ያደረገው መሲ አሽናፊ ኾኗል። አርጀንቲናዊ ኮከብ ክብሩን ለስምንተኛ ጊዜ በማግኘትም ቀዳሚ ተጫዋች መኾን ችሏል።
በሴቶች ዘርፍ ስፔናዊቷ አይታና ቦንማንቲ አሸናፊ ስትኾን የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና መወጣቷ ለክብሩ አብቅቷታል ተብሏል። ተጫዋቿ ከባርሴሎና ጋር የሴቶች የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ናት።
በሌላ በኩል የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለሆኑ ተጫዋቾች የሚሰጠውን “የገርድ ሙለር” ሽልማት ሲያሸንፍ፣ ከአርጀንቲና ጋር የዓለም ዋንጫን ያነሳው የአስቶን ቪላው ግብ ጠባቂ ኤሚ ማርቲኔዝ ለምርጥ ግብ ጠባቂ የሚሰጠውን “የያሲን ትሮፊ” አሸናፊ ሆኗል።
በሪያል ማድሪድ ቤት ድንቅ ጅማሮን እያደረገ የሚገኘው እንግሊዛዊ ጁድ ቤልንግሃም የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በሚልም አሸንፏል።
ትልቅ ክብር የሚሰጠውን እና በበጎ አድርጎት ላይ ለተሳተፉ ተጫዋቾች የሚሰጠውን ክብር ብራዚላዊ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ቪኒሺየስ ጁኒየር አሸንፏል። ተጫዋቹ ለክብሩ የበቃው በሀገሩ ብራዚል በችግር ምክንያት መማር ያልቻሉ ልጆችን በማገዝ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ በማድረጉ ነው ሲል ቢቢሲ ጽፏል።
ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ በዓመቱ ሦስት ዋንጫዎችን ያሳካው ማንቸስተር ሲቲም የዓመቱ ምርጥ ክለብ ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!