“ሰላም ከሌለ ምርትን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ስለማይቻል አምራቹም ኾነ ተጠቃሚው ተጎጂ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

49

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ፣ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ የንግድ ማዕከላትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከተመለከቷቸው የንግድ ማዕከላት ውስጥ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፣ የነጃጅ ማደያዎች እና የወተት እና ወተት ተዋጽኦ ችርቻሮዎች ይገኙበታል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የሸማቾች ማኅበራት በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ለማቅረብ ሁነኛ አማራጮች ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ማኅበራት የበለጠ ማደግ እና በአይነታቸው በርካታ ሸቀጦችን ማቅረብ እንዲችሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ዶክተር አሕመዲን ገልጸዋል።

ምርት እንደልብ ተዘዋውሮ ለተጠቃሚው እንዲደርስ እና የኑሮ ውድነቱም እንዲሻሻል የክልሉ ሰላም አስተማማኝ መኾን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።

“ሰላም ከሌለ ምርትን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ስለማይቻል አምራቹም ኾነ ተጠቃሚው ተጎጅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ስለዚህ በአንድነት ቁሞ ለክልሉ ሰላም መሥራት ከሁሉም አካላት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) የተለያዩ መሰረታዊ ሸቀጦች ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሱ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።

መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ የሚያስገባው ነዳጅ በአግባቡ ለተገልጋዩ እንዲደርስ ቴሌ ብርን በመጠቀም ዘመናዊ ግብይት ተዘርግቷል ሲሉም ተናግረዋል።

ይህም አላስፈላጊ የነዳጅ ክምችት እና ምርቱን ለማግኘት የሚደረገውን አሰልች ወረፋ ያስቀረ ነው ብለዋል።

የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተመጣጣኝ ዋጋ መሰረታዊ ሸቀጦችን እንዲያቀርቡ ለማስቻል ድጋፍ እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል።

ለአብነትም በ2015 ዓ.ም 497 ሚሊየን ብር ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በብድር መልኩ የተሰጠ መኾኑን አስታውሰዋል። በ2016 ዓ.ም ደግሞ እስካሁን ድረስ 110 ሚሊዮን ብር መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የወተት ኅብረት ሥራ ማኅበራትም ለክልሉ ኢኮኖሚ ዋነኛ ድጋፍ ስለመኾናቸው ዶክተር ኢብራሂም ተናግረዋል።
በክልሉ በርካታ የወተት ሃብት እንዳለ ጠቁመው ከክልሉ ከተሞች አልፎ ወደ አዲስ አበባም እየቀረበ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅማቸውን የበለጠ እያጎለበቱ የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ተግባር ላይ ጉልህ ሚና መጫዎት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ይህ እንዲኾን ደግሞ ንግድ ቢሮው ለማኅበራቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በመኸር ከአምስት ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleሊዮኔል ሜሲ ለስምንተኛ ጊዜ የባሎን ደ’ኦር አሸናፊ ኾነ።