
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ክልሉ የገቢ አቅምን በማሳደግ የሕዝብ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እቅድ ይዟል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ግን በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ መሰብሰብ እንዳይችል እንቅፋት እንደኾነበት ተገልጿል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ የሰላም እጦት ለገቢ አሰባሰብ ሥራው ፈታኝ መኾኑን አመላክተዋል።
የገቢ አሰባሰብን ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዝቡ ለገቢ አሰባሰብ ሥራ ለሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎች ከለላ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
የንግድና ማኅበራት ምክር ቤት ፣የነጋዴ ሴቶች እና ሌሎች ማኅበራት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው እንደተቋም ፍትሐዊነት እንዳይዛባና በንግዱ ማኅበረሰብም ያልተገባ ጥያቄ እንዳይነሳ ድልድይ ኾነው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
አርዓያነት ያለው ተግባር እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢዎች የተሻለ ክልል እና ሀገር እንዲኖር ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለገቢ አሰባሰቡ የበሉላቸውን ድርሻ አንዲወጡም አሳስበዋል።
ገቢ መሰብሰብ ያልቻለ መንግሥት የዜጎችን ጥያቄ መመለስ እንደማይቻለውም ተናግረዋል።
ቢናገር የሚደመጥ ፣ለሚሠራው ሥራ አስፈላጊው ሁሉ የሚሟላለት ክልል እንዲኾን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የሚሰበሰበው ግብር የጋራ ሀብት መኾኑን በማሰብ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ወረቀት ላይ የተቀመጠውን እቅድ ወደ ገንዘብ ለመቀየር የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃልም ብለዋል።
በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት እንኳን ግብር ለመሰብሰብ ወላድ እናቶችን እንኳን ወደ ሕክምና ተቋም ለመውሰድ አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱን ነው የተናገሩት።
ለክልሉ የሚጠቅመው ኢኮኖሚን ማሳደግ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከዚያ ውጭ ያሉት አካሄዶች ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳውም አመላክተዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ ተንቀሳቅሶ ሳይሠራ ፣ ኢኮኖሚ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ተወዳዳሪ ሳይኾን ሲቀር ደካማ የኾነ ክልል ይፈጠራል ነው ያሉት።
ቆም ብሎ በማሰብ ለነፃ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የበኩልን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት ይመጡ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አሁን ላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፋብሪካቸውን ነቅለው ላለመሄዳቸው ማረጋገጫ የለም ነው ያሉት።
የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በቀነሱ ቁጥር የክልሉ ኢኮኖሚ እንደሚወድቅም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ውድቀት ለአኹኑ ብቻ ሳይኾን ለቀጣዩ ትውልድም መጥፎ ጠባሳ እንደሚኾን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!