
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአብክመ ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 240/2008 የታክስ አሥተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 መሰረት የግብር ውሳኔ ከተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ያልተከፈለ ገቢ ውዝፍ ግብር እንደሚባል ተቀምጧል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ በ2015 በጀት ዓመት 33 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 23 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም አስታውቋል።
በመምሪያው የታክስ ዕዳ ክትትል ባለሙያ ወይዘሮ ወርቄ ፅጌ በ2016 በጀት ዓመት 27 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት 3 ሚሊዮን 409 ሺህ ብር ከ72 ግብር ከፋዮች መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ገቢ በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው አንጻር ዝቅተኛ መኾኑን የገለጹት ባለሙያዋ ለዝቅተኛ አፈጻጸሙ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም እጦት በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
የውዝፍ መዝገብ ምርመራው በወቅቱ መከናወኑን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ግብርን በወቅቱ በመክፈል ውዝፍ ግብር ይዟቸው ከሚመጡ ተያያዥ ችግሮች ራስን መታደግ አስፈላጊ ነው ሲሉ መልእክታቸውንም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!