
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፈተኛ ጫና ፈጥሯል ተብሏል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ የቢሮውን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአማራ ክልል የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ ጀምሮ የሰላም እጦት መከሰቱን ተናግረዋል።
የሰላም እጦቱም በገቢ አሰባሰብ ሥራው ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።
የገቢ ሥራው መሰናከል ሲያጋጥመው መሠረታዊ ተቋማት ዝግ እንደሚኾኑም ተናግረዋል።
የገቢን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት መሥራት ይገባልም ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ የክልሉ የገቢዎች መዋቅር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች እየተገኙ ሥራቸውን እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
“ግብር የዜግነት ክብር” በሚል መሪ ሃሳብ ወደ ሥራ መግባታቸውን ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኀላፈው የሰላም እጦቱ በአሰብነው ልክ እንዳንጓዝ አድርጎናል ብለዋል።
በሰላም እጦቱ ምክንያት በሩብ ዓመቱ 17 ነጥብ 9 በሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅደው 6 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰባቸውንም ተናግረዋል።
ከእቅዱ የ11 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ጉድለት መኖሩንም አመላክተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሰብስበው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።
ካበለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ 2 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር መቀነስ አሳይቷልም ብለዋል።
በበጀት ዓመት የታቀደውን ለማሳካት የመደበኛ የቁርጥ ግብር ጥናት አንደኛው እንደነበር ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው 449 ሺህ 793 የሚኾኑ ግብር ከፋዮችን ለማጥናት አቅደው 406 ሺህ 964 ግብር ከፋዮችን ማጥናታቸውን ነው የተናገሩት።
ክልሉ ውስጥ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ከማጥናት ያለፈ ማስከፈል አለመቻላቸውንም አስታውቀዋል።
የቁርጥ ግብር ጥናት የክልሉን የገቢ አፈፃፀም ሊያሻሽል እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበት እንደነበርም ተናግረዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ችግሮችን ተቋቁመው የተሻለ ግብር መሰብሰባቸውንም አስታውቀዋል።
የገቢ እቅድን ማሳካት ካልቻልን ከጥቂት ወራት በኋላ ደሞዝ ለመክፈል አዳጋች ሊኾን እንደሚችልም አመላክተዋል።
ክልሉ ግብር የመሰብሰብ አቅም አለው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አርበኞች መኾን ካለብን ድኅነት ላይ አርበኞች መኾን ይገባል ብለዋል።
ሕዝብን ከችግር ውስጥ ለማውጣት ጀግኖች መኾን እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በአስተውሎት በመመልከት ለሰላም ዋጋ መስጠት እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የሰላም ተግዳሮት ውስጥ የሚፈተነው ተቋም የገቢ መዋቅሩ መኾኑንም አመላክተዋል።
የሚከፈለው ግብር ለክልሉ ሕዝብ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈታበት መኾኑን በማወቅ ለተፈፃሚነቱ የድርሻን መወጣት ይገባል ብለዋል።
ሕዝቡም በየደረጃው ለሚገኘው መዋቅር ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!