
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማን መሰረተ ልማት በማሳደግና የመኖሪያ ቤት ችግርን በመፍታት ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የከተማውን መሰረተ ልማት ለማስፋፋት፣ የሥራ አጥነትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የከተማውን ገቢ አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ገቢ ሲሰበሰብ የከተማው መሠረተ ልማት ይፋጠናል፤ ሌሎችም የከተማውን ውበት እና ዘመናዊነት የሚያሳድጉ ሥራዎች መሥራት ያስችለናል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገቢን የማሳደግ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የቤት ልማት ሥራው አማራጨ-ብዙ እንዲኾን ማድረግ ሌላኛው ትኩረት የሚሰጠው መኾኑን ገልጸዋል።
ለመኖሪያ ቤት ሥራ የተደራጁ ማኅበራት የቦታ ሽንሸና እና ዕጣ ወጥቶ ማለቁንና በወቅታዊ ችግር ምክንያት ታግዶ የነበረው የግንባታ ፈቃድ ሥራ መለቀቁን ጠቁመዋል።
በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ማግኘት ይገባቸዋል ተብለው የተለዩ ሰዎች የግንባታ ፈቃድ በቅርቡ እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ያሉት።
መስፈርቱን ሳያሟሉ የተደራጁ አሉ በሚል የቀረበ ቅሬታም በመኖሩ በቅሬታ ሥርዓቱ ታይቶ እንደሚፈታ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
”አሁንም ተደራጅቶ መሬት ለማግኘት የሚፈልገው ብዙ በመኾኑ ከክልሉ መንግሥት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልገናል” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መሬት ካገኙ በኋላ ሠርተው የቤት ባለቤት መኾን ሳይችሉ የሚቀሩትም በርካታ መኾናቸውን አንስተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው “ዜጎች በአቅማቸው ልክ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚኾኑበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል” ብለዋል።
የከተማውን መሬት የማቅረብ አቅምን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደ አማራጭ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።
ከባንኮችና አበዳሪ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የገንዘብ እጥረትን ለመቅረፍ እንሠራለን ብለዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመትና በቀጣይ ጊዜያት ከክልሉ መንግሥት እና ከከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ጋር በመነጋገር አማራጮችን በማስፋት ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እንደሚሠራ ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!