ማኅበረሰቡ የራሱ መገለጫ የኾኑ ቅርሶችን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ።

49

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረሰቡ መገለጫ የኾኑ ተፈጥሯዊ ፣ታሪካዊ እና ባሕላዊ ቅርሶች በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ ገልጸዋል። ኀላፊው እንዳሉት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት በተለይም ደግሞ በምሥራቁ የክልሉ ክፍል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶችን በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና በፌዴራል መንግሥት በኩል ጥገና ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ስለመደረጉ ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ጥገና እየተደረገላቸው የሚገኙ ቅርሶች መኖራቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ ከሚገኙት ዓለም አቀፍ ቅርሶች ውስጥ

የጎንደር አብያተ መንግሥታት በፌዴራል ደረጃ በቀጣይ ወራት ወደ እድሳት ለመግባት የሚያስችል ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል። ከጎንደር አብያተ መንግሥታት ውስጥ አንዱ የኾነው የጉዛራ ቤተመንግሥትም የ35 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት በፌዴራል ቅርስ ባለሥልጣን እየተጠገነ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት እንዲጠናቀቅም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትንም በዘላቂነት ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም ደግሞ አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች የማደስ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።

ከፍተኛ እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶችን አስመልክቶ ጥናት ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ከዓለም ዓቀፍ ቅርሶች ባለፈ በክልሉ የተመዘገቡ ቅርሶችም ጊዜያዊ እድሳት እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አቶ ጣሂር ገልጸዋል። በ2014 በጀት ዓመት 42 ቅርሶች ፣በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ 33 ቅርሶች በክልሉ መንግሥትና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ጊዜያዊ ጥገና መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል።

ይሁን እንጅ በበጀት እጥረት ምክንያት ክልሉ ካለው ሰፊ ቅርስ አኳያ በሚጠበቀው ልክ ጥገና ማካሄድ አለመቻሉን ነግረውናል። በቀጣይ መንግሥት ከሚመድበው በጀት ባለፈ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመዘርጋት እና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ቅርሶችን ለማደስ ትኩረት ተደርጓል።

ማኅበረሰቡም ቅርሶችን የመጠበቅ ታሪካዊ አደራውን እንዲወጣም ጠይቀዋል። ቅርሶች የሀገርን ታሪክ እና ማንነት የያዙ መኾኑን በመረዳት ከጉዳት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም በሚችለው መንገድ መረባረብ አለበት ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ባሰብኩት ልክ ገቢ እንዳልሰበስብ አድርጎኛል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ
Next article“ዜጎች በአቅማቸው ልክ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚኾኑበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው