“በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ባሰብኩት ልክ ገቢ እንዳልሰበስብ አድርጎኛል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ

52

ባሕርዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት በተቋማት መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ጫና መፍጠሩ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል። የሰላም እጦቱ ማኅበራዊ ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን እንዳይከውኑ፣ ገቢ የሚሰበስቡ ተቋማትም በተፈለገው ልክ ገቢ እንዳይሰበስቡ አድርጓቸዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ የሩብ ዓመቱን የገቢ አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው “የተከሰተው የሰላም እጦትም ገቢን ለመሰብብ እንቅፋት ኾኖብናል” ብለዋል። ሰላም ለገቢ ሥራችን እንደ ኦክስጅን ነው ሲሉም ተናግረዋል። ገቢ ያለ ሰላም ሰላምም ያለ ገቢ ትርጉም አልባ ድካም መኾኑንም ገልፀዋል። ገቢ ለአንዲት ሀገር ሕዝብ የሕልውና ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የሕዝብን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚያስችልም ገልፀዋል። ያለ ገቢ ልማትና እድገትን ማሰብ እንደማይቻልም አመላክተዋል።

ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ካልተቻለ የሕክምና፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ተግባራት፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ፣ የጸጥታ መዋቅር፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት እንደሚቆሙም ገልፀዋል። ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እስካልተቻለ ድረስ የክልሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ እንደሚወድቅም ተናግረዋል። በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መውደቅ ሲያጋጥም የሕዝብ ሥነ ልቡና እንደሚጎዳም ገልፀዋል።

ክልሉ በጀት ዓመቱ ወሳኝ ተግባራትን ለመከወን፣ የመልካም አሥተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ሥራ መጀመሩንም አስታውሰዋል። ገቢ ለመሰብሰብ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ከውነው እንደነበር ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ባሰብነው መንገድ እንዳንጓዝ አድርጎናልም ብለዋል። ከሰላም እጦቱ ባለፈ የቁርጥ ግብር ጥናት አፈፃፀም በተፈለገው ልክ አለመሄድ ለገቢ አሰባሰቡ ሌላ ችግር መፍጠሩን ነው የገለፁት።

በመኾኑም ሕዝብ የሚያስብ አካል በሙሉ በአንድነት ቁሞ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መሥራት አለበት ሲሉ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑም ሀገርም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው ተባለ።
Next articleማኅበረሰቡ የራሱ መገለጫ የኾኑ ቅርሶችን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ።