የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑም ሀገርም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው ተባለ።

51

አዲስ አበባ: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የ2015 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርትና የ2016 ዓ.ም እቅድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም የምርጫ ጉባኤ ያልተካፈሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የአፋር እና የትግራይ ክልል የማሟያ ምርጫ ይደረጋል ።

በተሻሻለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ላይም ጉባዔው ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ በእግር ኳሱ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን እና መቀረፍ ያለባቸውን ጉዳዮች በግልጽ በማንሳት ለተሻለ ሥራ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑም ሀገርም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መኾኑን አንስተዋል።

ብሔራዊ ቡድን የሀገር አርማ ነው ያለት አቶ ኢሳያስ ጂራ መንግሥት ከድጋፍ ወጦ ራሱን የቻለ በጀት መመደብ አለበት ብለዋል።

ክለቦች አደረጃጀታቸውን ማዘመን እንዳለባቸው የገለጹት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አስፈላጊውን የክለብ ፈቃድ ደረጃ እንዲያሟሉ ወደ አስገዳጅ ተግባር ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል ሜዳ ባለቤት አለመኾናቸው ለሀገር ክብር የማይመጥን ነው ያሉት በባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል ።

የክለቦች አደረጃጀት በፊፋና በካፍ ስታንዳርድ መዘመን እንዳለበት የተናገሩት ሚኒስቴር ዴኤታው በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በኩል ካለው የእግር ኳሱ እድገት ጋር የማይጣጣም ከፍተኛ ወጪን መያዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

በዚህ ላይ ክለቦች ግልጽ ውይይት ማድረግ እዳለባቸውም ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next article“በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ባሰብኩት ልክ ገቢ እንዳልሰበስብ አድርጎኛል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ