“96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

53

አዲስ አበባ: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሦስት ወራት 350 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች መሸፈን መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናግረዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ የሚወስዱ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ ሰነድ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አምራች የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካለት ጋር ምክከር እያደረገ ነው።

በዚህ የስትራቴጂክ ሰነድ ውይይት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የወጭ እና የገቢ ንግድ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት ነው ብለዋል።

የወጭ ንግድ ከ5 ቢሊዮን የማይበልጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የገቢ ንግዱ ደግሞ 15 ቢሊዮን ገደማ ይደርሳል። ይህም የንግድ ሚዛኑ በአብዛኛው ከፍተኛ ጉድለት ያለበት እንደኾነ ማሳያ እንደኾነ አንስተዋል።

የዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በሀገር ውስጥ በቂ እና ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ምርቶች አለማምረታችን ነው ብለዋል።

በዚህ ሁኔታ ያለ ሀገር ከፍተኛ የኑሮ ውደነት እና የገበያ አለመረጋጋት እንደሚገጥመውም አስገንዝበዋል።

ሚኒስተትሩ እንዳሉት ይህንን ችግርም ለመፍታት አንድ ዓመት የወሰደ ጥናት ተደርጎ “96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

ይህ የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ የሀገሪቱን የጥቅል ገበያ ምጣኔ ሃብት ማረጋጊያ አንድ ስልት መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ በንግግራቸው “ባለፉት ሦስት ዓመታት 350 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች መሸፈን ተችሏልም” ብለዋል።

በተዘጋጀው የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ስትራቴጂ ዙሪያ ግብዓት ለመሰብሰብ እና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የሦስት ቀናት ምክክር ተጀምሯል ተብሏል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም ዕትም
Next articleየካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑም ሀገርም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው ተባለ።