“የልማት ድርጅቶች ውድድርን በመፍጠር ትርፋማነታቸውን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

47

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2016 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የተሰጡበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ፣ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና የልማት ድርጅቶቹ የቦርድና የሥራ አስፈጻሚ መሪዎች ተገኝተዋል።

ለውይይት በቀረበው ሪፖርት ድርጅቶቹ ባለፈው በጀት ዓመት ያጋጠሟቸውን ማነቆዎች ተቋቁመው ትርፋማ ለመኾን ጥረት ማድረጋቸው ተነስቷል። ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውንም ለመወጣት መሥራታቸው ተገልጿል።

የአማራ ዉኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮንሥትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ እምሬ ኮርፖሬሽናቸው ባለፈው በጀት ዓመት የሲሚንቶ ችግር ማነቆ ኾኖበት እንደቆየ ጠቅሰዋል።

የልማት ድርጅቶች ውጤታማ ኾነው በልማታቸው ሕዝብ እንዲጠቀም የበጀት እጥረት መፈታት እንዳለበት አቶ ኤርሚያስ አሳስበዋል። የጸጥታ መደፍረስም በልማት ሥራዎቹ ላይ ከፍተኛ ማነቆ ስለኾነ ሁሉም ለሰላም ከልቡ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር አበባው ጌቴ ድርጅቶቹ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለግሮችም መፍትሔ በመኾን እያገዙ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ በክልሉ የተከሰተው ጦርነትና ግጭት ፣ የውጪ ምንዛሬና የብድር እጥረት እንዲሁም የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ለድርጅቶቹ ከፍተኛ ማነቆ መኾኑንም ነው አቶ አበባው የገለጹት።

አቶ አበባው ኪሣራ ውስጥ የነበሩት ድርጅቶች ከኪሳራ ወጥተው በማገገም ላይ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። የጸጥታ ችግር በሌለባቸው የክልሉ አካባቢዎች በመሥራት ትርፋማነታቸውን እንዲያስቀጥሉ ጠንካራ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በውይይቱ ችግሮችን ለማለፍ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውና ወደ ሥራ መገባቱ ተጠቅሷል። ለዘላቂ ውጤታማነትም በድርጅቶቹ የተጠያቂነት እና የማበረታቻ አሠራር መተግበር እንዳለበት ተጠቁሟል።

ድርጅቶቹ ከአማራ ክልል አልፈው በሌሎች አካባቢዎችም ተወዳዳሪና የልማት ተሳታፊ መኾን እንዳለባቸው ተወስቷል። ሰላም በኾኑ አካባቢዎች በመሥራት ችግሮች የተከሰቱባቸው ፕሮጀክቶችን ድክመት ማካካስ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የልማት ድርጅቶቹ ችግሮችን አልፈው ስኬታማ ለመኾን የሚመሩበትን ራዕይ በማስተካከል የሰው ኀይልና የማሽኖቻቸውን ምርታማነት ማሳደግ ይገባል ተብሏል። እርስ በርስ መደጋገፍና የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማዘመንም ለውጤታማነት ያበቃሉ ከተባሉ አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ትርፋማነት ብቻ ለተቋሞቹ ቀጣይነት ወሳኝ በመኾኑ ውድድርን መፍጠርና አሸናፊ መኾን ይገባል ብለዋል። ለዚህም የነጋዴነት ባሕሪ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ የመሥራት አቅምን እና አሠራርን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ማሳደግ ድርጅቶቹ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ አብዱ ጠቅሰዋል።

የልማት ድርጅቶቹ ሥራ አስፈጻሚና ሥራ አመራር ቦርድም ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተወዳዳሪና ቀጣይ የልማት ድርጅት መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላዩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ መኾኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም ዕትም