በክልሉ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላዩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ መኾኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።

48

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚታረሰው አጠቃላይ መሬት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚኾነው መሬት በከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መኾኑን ግብርና ቢሮው ገልጿል። የአፈር አሲዳማነት በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ካልሲየም፣ ሶዲየም፣ ማግኒዝየም እና ፖታሽየም የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ታጥበው ሲያልቁ እና በምትኩ እንደ አሉሙኒየም፣ ሃይድሮጅን እና ብረት የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች በአፈር ውስጥ ሲከማቹ የሚፈጠር ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ሊታረስ ከሚችለው 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 43 በመቶው በአሲዳማነት ተጠቅቷል። ከዚህም ውስጥ 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ነው። የአፈር አሲዳማነቱ ሽፋንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።

በሀገሪቱ በጠንካራ የአፈር አሲዳማነት ደረጃ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙና ቀደም ሲል በምርታማነታቸውም የተሻሉ የነበሩ ናቸው። አሁን ላይ ደግሞ በስፋት ያመርቷቸው የነበሩ እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ የመሳሰሉ ሰብሎች ምርታማነታቸው ቀንሷል። ችግሩ በተባባሰባቸው ቦታዎች ደግሞ ከምርት ውጭ መኾኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቸው እንዳሉት ደግሞ የአፈር አሲዳማነት በአማራ ክልልም ፈተና እየኾነ መጥቷል። በሰብል ምርታማነት የሚታወቀው ምዕራቡ የክልሉ ክፍል በአሲዳማነት ተጠቅቷል። ከፍተኛ ስንዴ አምራች የኾኑ እንደ ወምበርማ እና ደብረ ኤሊያስ የመሳሰሉ ወረዳዎች ጭምር በከፍተኛ አሲዳማነት መጠቃታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።

አሁን ላይ ምሥራቁ የክልሉ ክፍል ጭምር በችግሩ መጋለጡ ተነስቷል፡፡ በክልሉ ከሚታረሰው 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ በመካከለኛ አሲዳማነት ተጠቅቷል፡፡

የአፈር መሸርሸር እና በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መጠቀም ለችግሩ በምክንያትነት ተቀምጠዋል። የመሬት በተከታታይ መታረስ እና በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ሰብል ማምረትና ሌሎችም የአፈር አሲዳማነት ምክንያቶች እንደኾኑ ተነስቷል፡፡
በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬት በምርታማነት ላይ ከ50 በመቶ ይቀንሳል። ችግሩ የባሰ ሲኾንም ከምርት ውጭ መኾንን እንደሚያስከትል ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡

ውጤታማ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በመሥራት፣ የደን ሽፋንን በማጠናከር እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የአፈር አሲዳማነትን መከላከል እንደሚቻል ባለሙያው ተናግረዋል። ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ኖራን ከመጠቀም ባለፈ አሲዳማነትን መቋቋም በሚችሉ የሻይ እና ቡና ተክል መሸፈን ሌላው መፍትሔ እንደኾነ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በወቅቱ የነበሩት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ለአሚኮ እንደገለጹት በአማራ ክልል 10 ዞኖች የሚገኙ 100 ወረዳዎች በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው፡፡

በክልሉ በከፍተኛ አሲዳማነት ከተጠቃው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከ6ዐዐ ሺህ በላይ ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት ምክንያት ምንም ዓይነት ምርት እንደማይሰጥ ገልጸዋል።

ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ደግሞ ከፍተኛ የአሲዳማነት ችግር እንዳለባቸው ማንሳታቸው ይታወሳል።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግብርና፣ በኢንዱሥትሪ እና ምህንድስና ዘርፍ ተሰማርተው ሃብት የሚያመነጩ የልማት ድርጅቶችን በትኩረት እንደግፋለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የልማት ድርጅቶች ውድድርን በመፍጠር ትርፋማነታቸውን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን