
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2016 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ግምገማ እና ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በውይይቱ ተገኝተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ የልማት ድርጅቶቹ የልማት ክፍተትን በመሙላት የክልሉ የካፒታል እና የቴክኖሎጂ አቅም እንዲኾኑ ታስቦ መቋቋማቸውን ጠቅሰዋል።
አንዳንድ ድርጅቶች አነስተኛ ውጤት የሚታይባቸውና እየተደገፉ የሚሠሩ መኾናቸው አዋጪ እንዳልኾነ ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። እነዚህ የልማት ድርጅቶች አትራፊ ኾነው ለክልሉ ተጨማሪ አቅም ከመኾን ይልቅ ኪሳራ ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ጥሪት ጭምር የሚያሟጥጡ ኾነው ተገኝተዋል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ከአቅም በላይ ለኾኑ ችግሮች ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የድርጅቶቹ አመራሮች እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በጥብቅ ክትትል የሚመራ የሥራ ባሕል መገንባት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ድርጅቶቹ ስኬታቸውን ከዕቅድ ክንውን ይልቅ በጠንካራ ተወዳዳሪነት መለካት እንዳለባቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመደጋገፍ እንደ መሬት፣ የውጪ ምንዛሪ እና የሲሚንቶ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የትኩረት መስክ የኾኑ ተቋማትን ለይቶ ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ “በግብርና፣ በኢንዱሥትሪ እና ምህንድስና ዘርፍ ተሰማርተው ሃብት የሚያመነጩ የልማት ድርጅቶችን በትኩረት እንደግፋለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!