“የምንፈጽመውን ብቻ እንናገራለን፤ የተናገርነውን እንፈጽማለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ

45

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ደሴ ከተማ ሰላሟን ጠብቃ ልማት ላይ ናት። የከተማዋ ነዋሪዎች ከምንም በላይ ሰላምና ልማትን አስቀድመዋል። ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ይሻሉ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የከንቲባ ችሎት መዘርጋታችን እና ለፍትሕ በመሥራታችን ከሕዝብ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጓል ብለዋል።

የደሴን የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዛቸውም ከሕዝብ ጋር የበለጠ እንዲግባቡ እንዳደረጋቸው ነው የተናገሩት። በከተማዋ በርከት ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከተማዋ አስፓልት የሚመረትበት ማሽን( አስፓልት ፕላንት) እንዲኖራት ማድረግ ሌላኛው የተሠራው ሥራ መሆኑንም አመላክተዋል።

የአስፓልት ፕላንት ባለቤት መሆናቸው በከተማዋ ከጌጠኛ ድንጋይ ይልቅ አስፓልት እንዲሠሩ እንደሚያደርጋቸውና በቀጣናው ያሉ ከተሞች እንዲያለሙ እድል እንደፈጠረም ተናግረዋል።

ከሌሎች ከተሞች ጋር ተያይዞ የማደግ እድል መፍጠሩንም ገልፀዋል። በከተማዋ መሠረተ ልማት ላይ የሚሠራ ተቋራጭ ድርጅት ለማቋቋም እየሠሩ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በአንድ በጀት ዓመት ብቻ በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውንም ተናግረዋል። ከሕዝቡ ጋር በተፈጠረው መልካም ግንኙነት እና አንድነት ሕዝቡ ቢሮ ገንብቶ እስከማስረከብ እንዳደረሰውም ገልፀዋል።

ደሴ የሰላምና የልማት ከተማ እንድትሆን ሕዝቡ ከጎናችን ኾኖ አግዞናልም ብለዋል። በከተማ አስተዳደሩ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ሕዝቡን ጥሩ ተስፋ እንዲረው እና እንዲረካ እያደረገው መኾኑንም ተናግረዋል።

ከተማዋ ሰላም የኾነችው ሕዝቡ ቀና ትብብር በማድረጉ፤ ሰላም ወዳድ ሕዝብ በመሆኑ ነውም ብለዋል። የደሴ በአጠቃላይ የወሎ ሕዝብ የጦርነትን አስከፊነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰላም ወዳድ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል።

የሕዝቡ የፖለቲካ ግንዛቤም ከፍ ያለ መኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው የሚረዳና የሚያውቅ ነውም ብለዋል።

ደሴ ከተማ ሰላም ስትኾን ሕዝቡ ጥያቄ የለውም ማለት አይደለም፣ ጥያቄ አለው፣ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄ የጋራ ጥያቄዎቹ ናቸው፣ ነገር ግን ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ ይፈታሉ ብሎ ስለሚያምን ነውም ይላሉ።

ጥያቄዎቹ እንዲፈቱም የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት እንደሚያምንም ገልፀዋል። ከሁሉም አስቀድሞ ለሰው ልጆች ሰላም መሥራት እንደሚገባውም ያምናል ነው ያሉት።

የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ የተጀመሩ ልማቶች እንዲቆሙ አይፈልግምም ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላምና ልማት ይቀጥላል፣ የሕዝብ ጥያቄዎችም እንዲፈቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እንደሚሉም ገልፀዋል።

ለሕዝብ የሚመጥን ሥራ ለመሥራት ጥረት አድርገናል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሥራችንም ሕዝብ ከፈጣሪ ቀጥሎ እውነተኛ ዳኛ መሆኑን አይተንበታል ነው ያሉት።

የምትናገረውና የምትተገብረው ነገር አንድ ዓይነት ከሆነ ሕዝብ እንደሚደግፍ ያየንበት ነውም ብለዋል። ንግግርና ተግባር የተለያየ ከሆነ ግን ከሕዝብ ጋር ያጋጫል ነው ያሉት።

የምንፈጽመውን ብቻ እንናገራለን፤ የተናገርነውን እንፈጽማለንም ብለዋል። ሕዝብ የደገፈን ሁሉንም የደሴ ከተማዋ ነዋሪዎች ጥያቄ ፈትተን አይደለም የሚሉት ከንቲባው ጥያቄዎችን ለመፍታት የጀመርነው መንገድ ተስፋ ስለሰጠው ነውም ብለዋል።
ሕዝቡ እያደረገው ላለው መልካም ሥራ ሁሉ ለደሴ ከተማ ነዋሪዎች ምስጋና ያንስባቸዋል ነው ያሉት።

ከተማዋ የሰላምና የልማት ተምሳሌት ኾና እንድትቀጥል ነዋሪዎቿ ከመንግሥት ጎን ኾነው እየሠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በከተማዋ የተጀመሩ መልካም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Next article“በግብርና፣ በኢንዱሥትሪ እና ምህንድስና ዘርፍ ተሰማርተው ሃብት የሚያመነጩ የልማት ድርጅቶችን በትኩረት እንደግፋለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ