
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢና የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚስፈልግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
በአፍሪካ አመራር ልኅቀት አካዳሚ “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ስልጠናው የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያለችበት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ የመንግሥት አሥተዳደር እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ነባራዊ ኹኔታን የሚያስገነዝቡ ሃሳቦች በስልጠናው እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላትም በሚቀርቡ ጽሑፎች ላይ በሚደረጉ ምክክሮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ስልጠናውን በአጽንኦት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
በስልጠናው የሚቀርቡ ሃሳቦችም በሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ የጋራ አቋም እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የኢትዮጵያ እዳዎችን በመቅረፍ ወደ ምንዳና ሃብት ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችል የሃሳብና የተግባር አንድነት መፍጠርም የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።
በስልጠናው የሚቀርቡ ገንቢ እሳቤዎችም የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ለቀጣይ የድጋፍና ክትትል ስራዎቻቸው መሰረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምጣኔ ሃብት፣ የሰላምና ደህንነት፣ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ፣ የጊዜና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በስልጠናው እንደሚዳሰሱ ተናግረዋል።
“የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል አሰባሳቢ ትርክትና ብሔራዊ አርበኝነት መፍጠር ያስፈልጋል” ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ በስልጠናው ሀገራዊ ትርክት መፍጠር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፤ አካዳሚው ከነበረበት ሁኔታ ወጥቶ ብቃት ያለው የስልጠና ማዕከል ለማድረግ የተሰራውን ስኬታማ ስራ አድንቀዋል።
በቀጣይም የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የተቋማት ኀላፊዎች እና መሪዎችን ለማብቃትና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለዚህም የልህቀት አካዳሚውን በበጀት፣ በሰው ሃይልና በመሰረተ ልማት የተሟላ እንዲሆን የምክር ቤቱ ቀጣይነት ያለው እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀድሞው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ሀገራዊና ማኅበራዊ እዳዎችን ወደ ምንዳና ሃብት የመቀየር ታሪካዊ ኀላፊነት አለብን ብለዋል።
ለዚህም የተሰጡ ኀላፊነቶችን በብቃት በመወጣት ቀጣይነት ላለው የተቋም ግንባታ በትኩረት መሥራት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!