
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቼስተር ዩናይትድ ከማንቼስተር ሲቲ የዓለምን ትኩረት የሳበ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በኦልድ ትራፎርድ ይጠበቃል።
ማንቼስተር ዩናይትድ ዝነኛው የቀድሞ አሰልጣኙ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ኦልድ ትራፎርድን ከለቀቁ በኋላ ባሉት አስርት ዓመታት ውስጥ የቀድሞ ዝናውን እና አስፈሪነቱን የጠበቀ ክለብ መኾን አልቻለም።
ማንቼስተር ዩናይትድ ከማንቼስተር ሲቲ በ10 ዓመታት ውስጥ ያላቸው አማካይ የነጥብ ልዩነትም 16 ነጥብ 5 ነው። ሲቲ በኦልድ ትራፎርድ በጋርዲዮላ እየተመራ ስድስት ጊዜ አሸንፏል፡፡ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችንም አንስቷል።
ዛሬ በኦልድትራፎርድ ምሽት 12ⵓ30 ማንቼስተር ዩናይትድ ቢያሸንፍ እንኳ የጋርዲዮላ ቡድን አሁንም በሰንጠረዡ ከቴን ሃግ በላይ መኾኑ እሙን ነው፡፡
ሊጉን ቶተንሃም ሆትስፐር በ26 ነጥብ ሲመራ፣ አርሰናል በ24 ነጥብ ሁለተኛ፣ ማንቼስተር ሲቲ በ21 ነጥብ ሦስተኛ ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ከዘጠኝ ግጥሚያዎች አራት ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዶ በድምሩ በ15 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በ2023/24 የውድድር ዘመን ሁለት ጊዜ ከሜዳው ውጪ በዎልቨር ሃምፕተን ዋንደርስ እና በአርሰናል ሽንፈትን አስተናግዷል።
የሦስትዮሽ አሸናፊው ሲቲ ወደዚህ ውድድር የሚገባው በቻምፒየንስ ሊጉ ያንግ ቦይስን 3 ለ 1 አሸንፎ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድም በተመሳሳይ ውድድር ኮፐንሃገንን በማሸነፍ ቀጣይ ተስፋዉን ከፍ አድርጎ ነው።
እስካሁን ሁለቱ ክለቦች 190 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ማንቼስተር ዩናይትድ 78 ጊዜ ሲያሸንፍ ፤ በ53 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥተዋል። ቀሪዎቹን 59 ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ ድል አድርጓል፡፡
ፔፕ ከዛሬው 191ኛው ደርቢ በፊት በነበረ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳሉት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሲቲ ጠንካራውና አሸናፊው ቡድን ነው፡፡
የሰማያዊ ለባሾቹ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የተጫዋቾቼ ዓላማ እያንዳንዱን ጨዋታ አሸንፎ በሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ነው፡፡ ይህንንም ያደርጉታል፡፡ በሲቲ የ129 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማ ጊዜ ላይም እንገኛለንና ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን 2013 ላይ ክለቡን ከለቀቁ በኋላ ማንቼስተር ዩናይትድ የተለያዩ አሰልጣኞችን ቢቀያይርም ከሲቲ በልጦ ደጋፊዎችን ጮቤ ያስረገጠበት ታሪክ ማስመዝገብ ግን አልቻለም፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ከፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ የክለቡ የሃብት መጠን ማሽቆልቆሉ ስመ ጥር ተጫዋቾችን ለመግዛት እጅ ከወርች እንዳሰረው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡
የማንቼስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ “ቡድናችን ለማሸነፍ ወደምንፈልገው አቋም እየተመለሰ ነው፤ ስለዚህም እናሸንፋል፤ ጨዋታው ከሌሎች የደርቢ ግጥሚያ በላይ ነው ቢሆንም ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዛሬ ማንቼስተር ሲቲዎች የቀያይ ሰይጣኖቹን የሦስት ጨዋታዎች የማሸነፍ ጉዞ ያስቆሙት ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ዓይኖች ሁሉ ዛሬ ምሽት 12:30 ላይ በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ላይ ያተኩራሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!