“በደሴ ከተማ ለፍትሕ የቆመ ችሎት”

41

ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ፍርድ ተጓደለ፣ ደሃ ተበደለ የሚል መሪ በተገኘ ዘመን ሀገር ሰላም ትሆናለች፣ ልጆቿን በፍቅር እና በአንድነት ታሰባስባለች። የሀገሬው ሰው ሲጸልይ ” ፍርድ ተጓደለ፣ ደሃ ተበደለ የሚል መሪ አታሳጣን” ይላል። ደሃ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል የግፍ እንባ ይፈስሳል፣ የደሃ አንጀት በሀዘን ይቆረጣል፣ በሀገር ላይ ግፍ ይመጣልና። ፍርድ የማያጓድል፣ ደሃ የማይበድል መሪ በተሰጠም ጊዜ አምላኩን እያመሰገነ ይኖራል።

በዚያች ፍቅር በሚፈስስባት፣ መከባበር በሚደምቅባት፣ እንግዳ ተቀባይነት በበዛባት፣ የአንድነት ገመድ በጠበቀባት፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ኃያል ኾኖ በሚኖሩባት፣ ደስታ በመላባት፣ ሰላም በተጠበቀባት፣ ሃይማኖት በሚሰበክባት፣ እሴት በጸናባት፣ ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ በምትልባት፣ ሰውነት ከሁሉም ልቆ በሚታይባት፣ አብሮነት በእንቁ እንደተንቆጠቆጠ የክብር ካባ አምሮ በሚለበስባት ውብ ከተማ የቀደመው አልተረሳም፣ የጥንት የጠዋቱ አልተዘነጋም።

የጥንቱን እያውታወሰች፣ ዘመኑን እየዋጀች፣ ፍትሕን ታሰፍናለች፣ ፍርድ ታስተካክላለች፣ የበደለን እንዲክስ፣ የተበደለ እንዲካስ ታደርጋለች፣ የሠረቀን ታስመልሳለች፣ ያዘነን በፍትሕ ታፅናናለች፣ ተስፋ ያጣን በፍትሕ ተስፋውን ትመልሳለች፣ በእውነት የያዘውን በእውነት ትመልሳለች። በዚያች ከተማ ለፍትሕ የቆመ ችሎት አለና።

የቀደሙት ነገሥታት፣ መኳንንት፣ መሳፋንት፣ የጦር አበጋዞች፣ ሀገረ ገዢዎች እረኛው ምን አለ? አዝማሪስ ምን ተቀኘ? እያሉ ይጠይቁ ነበር አሉ። እረኞች እና አዝማሪዎች ሕዝብ ሲደሰት ደስታውን፣ ሕዝብም ሲከፋ መከፋቱን በቅኔ እያዋዙ ይቀኛሉና። እረኞች እና አዝማሪዎች የሕዝብን ብሶትና ደስታ ብቻም አይደለም የሚገልጹት ትንቢትም ይተነብያሉ ይሏቸዋል። እረኞችና አዝማሪዎች ያሉትን የሰሙ ነገሥታት በአፋጣኝ ውሳኔ ይወስናሉ፣ ለሕዝባቸውም የሚበጀውንና የተመቸውን ነገር ያደርጋሉ።

የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ መከፋትና መደሰት በእረኞች እና በአዝማሪዎች አማካኝነት እያወቁ ፍርድ ያስተካክላሉ። በኢትዮጵያ የኢጣልያ ጦርነት ወቅት እረኞች አዋጊዎች እንደነበሩም ይነገራል። ለአርበኞች ምስጢራዊ ጥቆማ በመስጠት፣ መንገድ በመምራት እና የጠላትን አቅም በማሳወቅ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ለአብነትም የኢጣልያ ፋሽስት ሠራዊት አርበኞቹ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀስ እረኞች በተራራ አናት ላይ ሆነው” ነጩ በሬ መጣልህ፣ ጥቁሩ በሬ ተጠንቀቅ” እያሉ አርበኞች እንዲጠነቀቁ እና የሚሄድባቸውን ጠላት ተዘጋጅተው እንዲጠብቁት ያደርጉ ነበር አሉ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ነገሥታቱ በተቀመጡበት ችሎት ማስቻል፣ የተበደለን እንዲካስ፣ የበደለ እንዲክስ ማድረግ የተለመደ ነበር። ይሄም አንድም ፍርድ እንዳይጓደል፣ ደኃ እንዳይበደል ሲያደርግ፣ ሁለትም ነገሥታቱን እና ሕዝቡን ያገናኛል፣ መሪና ተመሪውን አቀራርቦ ያስተዋውቃል። ይህ መሪዎቹ በተገኙባት ችሎት ማስቻል፣ ፍርድ ማስተካከል፣ የሕዝብን እንባ ማበስ፣ የተቀማችን ፍርድ ማስመለስ ከተተወ ቆይቶ ነበር። በታሪካዊቷ ከተማ በደሴ ግን ይህን ነገር አለ። መሪዎች እና ተመሪዎች ይገናኛሉ። ስለ ፍትሕም በጋራ ይነጋገራሉ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ችሎት የሚባል የቀደመውን ዘመን የሚያስታውስ፣ የብዙዎችን እንባ የሚያብስ ሥራ ከተጀመረ ሰነባብቷል። ይህም ተግባር እኒያ ፍቅርና ፍትሕ የሚያወቁ ነዋሪዎችን አስደስቷል። የችሎቱን ሀሳብ ያመነጩትን እና የተገበሩትን መሪዎችም አስሞግሷል፣ አስመስግኗል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲቢ ሳሙኤል ሞላልኝ የከንቲባ ችሎት የሕዝብ አገልግሎት የምንሰጥበት ቀን ነው ይሉታል። በከተማዋ ማክሰኞ እና ሐሙስ ቀናት ከንቲባው በተገኙበት ችሎት ይካሄዳል። ከንቲባው በመካከል ተቀምጠው በግራና በቀኝ አቤቱታ የሚበዛባቸው መሥሪያ ቤት መሪዎች ይቀመጣሉ። አቤቱታ አለኝ የሚሉ ደግሞ በወረፋ አማካኝነት በአዳራሽ ይታደማሉ። በችሎት ምን ዋለ የሚለውን ለማስማት የሚሹም ይመጣሉ። አቤቱታ ሲቀርብ፣ ለአቤቱታው የሚሰጠውን ምላሽም ያዳምጣሉ። የሚመለከታቸው ሁሉ በተገኙበት አቤቱታ ይቀርባል፣ የሕዝብ ጥያቄ ይነሳል። መሪዎችም አቤቱታዎችን ይሰማሉ።

በችሎቱ ውስጥ የታደሙት ሁሉ እውነተኛ አቤቱታ ያመጡት እውነተኛ ፍርድ ሲሰጣቸው፣ የተዛባ ነገር ያመጡም ልክ አለመሆናቸው ሲነገራቸው ይመለከታሉ። በችሎቱ ያዩትንም በየቀያቸው ይነጋገሩበታል። ይመካከሩበታል። በከንቲባ ችሎት ለዓመታት ፍትሕ የተጠሙ ፍትሕ አግኝተተዋል፣ ለዓመታት ያነቡ ተደስተዋል። ደኃም ሃብታምም ሳይመረጥ አቤቱታ ያላቸው ሁሉ ከንቲባውን ያገኛሉ። ከንቲባው ባሉበትም አቤት ይላሉ። በከንቲባ ችሎት ነገሮችን ማድበስበስ፣ መሸፋፈን፣ መዋሸት አይቻልም ነው የሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።

የከንቲባ ችሎት እጅ መንሻ የሚሹ ሁሉ የሚጋለጡበት፣ ሕዝብን የሚበድሉ፣ ፍርድ የሚያጓድሉ አደባባይ ላይ ከእነ ስህተቶቻቸው የሚታዩበት፣ መልካም የሚሠሩ የሚመሰገኑበት ነው። ከንቲባ ችሎት ማጋለጫ ነውም ይሉታል። ከንቲባ ችሎት ለማስጀመር ሲነሱ ከከተማዋ መሪዎች ጋር ፍትሕን ማረጋገጥ አለብን ብለን ተማምነን ነውም ብለውኛል። ሕዝብ ከምንም በላይ ፍትሕን ይሻል፣ ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ የመሪዎችና የአስተባባሪ ኮሚቴዎች አቋም እንደሆነም ነግረውኛል። የከተማዋ መሪዎች አንድነት መርህን መሠረት አድርጎ እንዲጠናከር አድረግን፣ አንድነት በመርህ ሲሆን ለብልሹ አሠራርም ኾነ ለመልካም አሠራር የጋራ አቋም ይኖረናል፣ ብልሹ አሠራርን በጋራ ታግለን እንጥላለን ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደነገሩን እርስ በእርሳቸው ቃል ኪዳን ተገባብተዋል፣ ቃለ መሃላም ፈፅመዋል። ችግሮች ሲገጥሙ ችግርን የሚተነትን መሪ ብቻ ሳይሆን የተደራጀ መፍትሔም የሚያመጣ መሆን አለበት፣ መሪነት በችግር ውስጥ ኾኖ የተሻለ ነገርን ማምጣት ነው፣ ምክንያት እየደረደሩ መቀመጥ አይደለም፣ ችግር ገጠመህ ምን መፍትሔ ወሰድህ? የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው፣ እኛም ችግሮችን እየተነተኑ መኖር አይቻልም፣ የመፍትሔ ሰዎች መሆን አለብን ብለን ተግባባን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። የውጤት መሪዎች እንዲኖሩ መግባባታቸውንና በተግባቡበት መሥመር መሥራታቸውን ነው የተናገሩት።

ባወራሁት ልክ ክብር ይገባኛል የሚል መሪ ሳይሆን በተገበርኩት ልክ ክብር ይገባኛል የሚል መሪ እንዲፈጠር ነበር የተግባባንም ይላሉ። ሌብነትን የሚጠየፍ፣ ሌብነትንም የሚከላከል መሪ እንዲፈጠርም ተግባብተው ሥራ መጀመራቸውን ነው የሚያስታውሱት። ሞራል የሌለው መሪ ይሠርቃልም ይላሉ። ታይቶ የማይታወቅ ችግር ሲገጥም ታይቶ የማይታወቅ መፍትሔ እናምጣ አልን፣ ከታች እስከ ላይ አንድ ሆን፣ መቶ በመቶ ባይሆንም ጥሩ ነገር ታዬ፣ ሁሉም በአቅሙ ሠራ፣ ለውጥም ታዬ ነው ያሉት።

የከንቲባ ችሎት የዜጎችን እንባ ያበስንበት፣ ፍትሕ ለተጠሙ ፍትሕ የሰጠንበት ነውም ይላሉ። የበደሉ ክሰዋል፣ የተበደሉ ተክሰዋል። በመሪዎች እና በሕዝብ መካከል ፍቅር እንዲኖር፣ መተባበርና መተማመን እንዲጎለብትም አድርጓል። ስርዓት ሲከበር ያየው ሕዝብ ለምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ አጋዥ ኾኖናል ይላሉ። በአቤቱታው አማካኝነት በችሎቱ የተወሰነው ውሳኔ መተግበሩን የሚያረጋግጥ ግብረ ኃይልም አለ። በግብረ ኃይሉ መሠረት ክትትል ይደረግበታል፣ ሳይፈፅም የቀረ መሪ ይጠቃል። ደሴ ላይ ከንቲባን ወይም ሌላን መሪ ደብቆ ውስጥ ለውስጥ ሥራ ሠርቶ ማምለጥ የሚችል የለም። ሁሉም ግልፅ ነው። በግል ይሠራል፣ በግልፅ ይዳኛል ይላሉ።

የቆዩትን ችግሮች ቀርፈን ባንጨርሳቸውም በእኛ ዘመን ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ማስቆም አለብን ብለን እየሠራን ነውም ብለዋል። የሚሠርቅ ወይም እጅ መንሻ የሚቀበል መሪና ባለሙያ የሚጠየቅበትን ሥርዓት ዘርግተናል፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የትም አያመልጥም ነው ያሉት። የከንቲባ ችሎት ያለ አግባብ መንግሥትና ሕዝብ የሚያጋጩትንም የሚያጋልጥ ነው። ጥሩ በማይሠሩት በጅምላ ሲወቀሱ የኖሩ ባለሙያዎች ታታሪነታቸውን የከንቲባ ችሎት አውጥቶላቸዋል፣ እነሱም ለበለጠ ሥራ እየተነሱ ሕዝብ እያገለገሉ መሆናቸውንም ነግረውኛል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደነገሩን የደሴ ከተማ ከንቲባ ችሎት በሀገር ደረጃ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት ተሞክሮ ኾኖ ቀርቧል። በደሴ ከተማ እየተተገበረ ያለው የከንቲባ ችሎት በሁሉም ከተሞች ቢተገበር ሕዝብና መንግሥትን በአንድ ጊዜ ያስተሳስራልም። የከንቲባ ችሎት ሕዝብን በፍትሕ ያረካልና። መሪዎች በከንቲባ ችሎት ለመቅረብ መጀመሪያ ንፁህ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፣ ካለበለዚያ ይዋረዳሉ፣ ላለመዋረድ በጥንቃቄ ይሠራሉ፣ መሪዎች እና ባለሙያዎች ንፁህ ሆነው እንዲመሩ፣ ሕዝብም ጥርጣሬ እንዳይኖረውም ያደርጋል ነው የሚሉት።

የከንቲባ ችሎትን ሲጀምሩ ፈተናዎች እንደነበሩባቸው የሚያስታውሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በትጋት በመሥራታቸው ከጉዟቸው አለመቆማቸውንም አንስተዋል። ሁሉም ወደ ከንቲባ ችሎት እንዳይመጣና ጊዜ እንዳይወስድ በየክፍለ ከተማው የሥራ አስፈፃሚ ችሎት አቋቋሙ። በሥራ አስፈፃሚ ችሎት ውሳኔ ያረካ ደግሞ በከንቲባ ችሎት ይቀርባል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ወደ ኀላፊነት የመጡበትን ዓላማ ሲናገሩ ወደ ከተማዋ የመጣሁት ለጥቅም አይደለም፣ የመጣሁት ታማኝ ኾኜ ለማገልገል ነው። በከተማዋ እስካሁን የመጡት ለውጦች የእኔ ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም መሪዎች እና ባለሙያዎች አንድነት፣ ከሕዝብ ጋር በተፈጠረ ቅንጅት ነው ይላሉ።

በከተማዋ በከንቲባነት በሚኖራቸው ቆይታ የተጀመረው መልካም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ጠንካራ የመንግሥት ተቋም እንዲፈጠር እሠራለሁ ነው ያሉት። ከኀላፊነት ብለቅ ክፍተት ሳይፈጠር የተደራጀ አሠራር እንዲኖር ጠንካራ ሥርዓት እዘረጋለሁም ብለዋል። ሊታዩ የሚችሉ የልማት ሥራዎች እንዲኖሩ እንደሚሠሩ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተጀመሩት ይጠናቀቃሉ፣ የተጠናቀቁት ሕዝብ ተረክቧቸው አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት። እኛ ሥራ ላይ ነን፣ በሥራችን እንቀጥላለንም ብለዋል። የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የተጠለብኝን ኀላፊነት እወጣለሁ ነው ያሉት። ለፍትሕ የተቋቋመው ችሎትም የበለጠ ያድጋል ይጠነክራል።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቱሪዝም መዳረሻዎች የጉብኝት ዋጋ መሻሻሉን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
Next articleተጠባቂው የማንቼስተር ደርቢ