ሁለተኛው የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ውጤት ላስመዘገቡ ክልሎችና ለመልካሳ ግብርና ምርምር ድጋፍ ተደረገ፡፡

52

አዲስ አበባ: ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በግብርና ሚኒስቴር ሁለተኛው የግብርና ዕድገት ፕሮግራም፣ በአየር ንብረት አፈጻጸም፣ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም እና የምግብና ሥርዓተ ምግብ ጽሕፈት ቤት ለክልሎች የመኪናና የሞተር ብሥክሌቶች እንዲሁም ለመልካሳ ግብርና ምርምር የተደረገ የቤተ-ሙከራ ዕቃዎች ድጋፍ ርክክብ ተደርጓል።

ድጋፎቹ የክልሎችን እና የከተማ አሥተዳደርን አቅም ለመገንባት የተደረገ መኾኑም ተገልጿል።

የምግብና ሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም የሥራ ኀላፊ ከበሩ በላይነህ የሁለተኛው የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ዓላማ በተመረጡ ወረዳዎች አነስተኛ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ ምርታማነት ማሳደግና ምቹ የገበያ ሁኔታ ለመፍጠር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የተሻለ ንጥረ ምግብ ይዘት ያላቸዉ የተለያዩ የሰብልና የእንስሳት ዓይነቶች በአርሶ አደሮች ማሣ እንዲመረቱ በማድረግ በቤተሰብ ደረጃ ያለዉን የአመጋገብ ሥርዓት ማሻሻል መኾኑንም ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ካስመዘገባቸው ውጤቶች መካከል በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተጠናው የሁለተኛው ምእራፍ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም መካከለኛ ዘመን ጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው:-
ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች በተጠናከረ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የተለያዩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ግብአቶችን የማቅረብ ፣ አዳዲስ የእንስሳት ዝሪያዎችን፣ የመስኖ ልማት አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በተጨማሪ የግብይት አገልግሎት ኹኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን በማከናወን ምርታማነት እንዲያድግና የአርሶ አደሮች የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲሻሻል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

በዚሁ መሠረት በፕሮግራሙ የታቀፉ አርሶ አደሮች ምርታቸዉ ከፕሮግራሙ በፊት ከነበረዉ፣ የሰብልና ጥራጥሬ ምርት በ18 በመቶ ፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በ45 በመቶ፤ የወተት ምርት በ39 በመቶ፤ የእንቁላል ምርት በ39 በመቶ፣ የማር ምርት በ78 በመቶ ለማሳደግ ተችሏል ብለዋል ኃላፊው ፡፡

የአርሶ አደሮችን ምርት ከገበያ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በመደረጉ የሰብልና ጥራጥሬ ምርት በ113 ነጥብ 5 በመቶ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ በ75 ነጥብ 5 በመቶ ፤ የወተት 204 ነጥብ 1በመቶ ፤ የማር ምርት 44 ነጥብ 6 በመቶ የእንቁላል ምርት 41 ነጥብ 9 በመቶ በማደጉ የአርሶ አደሩን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ከበሩ።

በአሁኑ ወቅት የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተቀርፆ በ10 ክልሎች፣ በ2 የከተማ አሥተዳደሮች፣ በ183 ወረዳዎች እና በ4 ሺህ 1 መቶ 30 ቀበሌዎች ላይ የትግበራ ሥራው መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በሁለቱ የግብርና ዕድገት ፕሮግራሞች ያልተሳተፉትንና በአዲሱ ያልተካተቱትን ወረዳዎች በግብርና ዕድገት ፕሮግራም የተገኘውን ውጤት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተጠናከሩ መልኩ እንዲቀጥሉ የቢሮ ኀላፊዎችና የወረዳ ተወካዮቹም በተገኙበት የተሽከርካሪ ድጋፎቹ ርክክብ ተደርጓል።

ከተደረጉ ድጋፎች መካከል:-

👉 ኦሮሚያ 30 መኪና ፣ 120 ሞተር ሳይክል

👉 አማራ 14 መኪና 50 ሞተር ሳይክል

👉 ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ 8 መኪና 30 ሞተር ሳይክል

👉 ደቡብ ኢትዮጵያ 7 መኪና ፣ 25 ሞተር ሳይክል

👉 ማእከላዊ ኢትዮጵያ 4 መኪና 10 ሞተር ሳይክል

👉 ትግራይ 5 መኪና 18 ሞተር ሳይክል

👉 ሲዳማ 2 መኪና 16 ሞተር ሳይክል

👉 ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 3 መኪና 10 ሞተር ሳይክል

👉 ጋምቤላ 2 መኪና ፣ 5 ሞተር ሳይክል

👉 ሀረሪ 1 መኪና ፤ 3 ሞተር ሳይክል

👉 ድሬደዋ 1 መኪና 3 ሞተር ሳይክል በዛሬው ሥነ-ሥርዓት ላይ በሚኒስትሩ ርክክብ ተደርጓል።

ለድገፉ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በድጋፉ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የተያዙትን ዕቅዶች በተነሳሽነት እንዲተገበሩ እና ድጋፎቹ ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ አሳስበዋል፡፡

የአየር ንብረት አፈጻጸም የመሬት አያያH ፕሮግራም በኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም ባንክ መካከል በተፈጸመ የ500 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ስምምነት መሠረት በአስር ክልሎችና በአንድ ከተማ አሥተዳዳር በተፋሰስ ልማት ሥራ እና በመሬት አሥተዳደር ሥራ ተከፋፍሎ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የዚህ ፕሮግራም ትግበራ ከዚህ በፊት ከሚታወቁ መሠል የፕሮጀክት ልምዶች በተለየ መልኩ የድህረ-ውጤት ልኬት ክፍያ አካሄድን የሚከተል ነው ፤ ይህም ማለት ከዓለም ባንክ ክፍያ የሚገኙ ሥራዎች ቀድመው ተከናውነው ያስገኙት ውጤት በገለልተኛ አካልም ተምግሞ ሲረጋገጥ ነው ተብሏል።

ዘጋቢ ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ ሥልጠና መሰጠት ተጀመረ።
Next articleየቱሪዝም መዳረሻዎች የጉብኝት ዋጋ መሻሻሉን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።