“የልማት ድርጅቶች በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ከመኾን ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካም የልኅቀት ማዕከል እስከመኾን የዘለቀ ራዕይ ሊከተሉ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

28

ባሕር ዳር:- ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አፈፃፀም እና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በአማራ ክልል 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ 13 የልማት ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2016 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ም/ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ጌቴ፣ የልማት ድርጅቶች የሥራ ኀላፊዎች እና የቦርድ አባላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አበባው ጌቴ ክልሉ በበርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል።

ድርጅቶች ኅልውናቸውን ከማስቀጠል ጀምሮ ለተቋቋሙለት ራዕይ ስኬት የሚያስፈልጓቸውን ድጋፎችም አንስተዋል።

ም/ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የልማት ድርጅቶች የገበያ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ የገበያ ፍላጎትን መፍጠር የሚችል አሠራር እንዲከተሉ እንዲሁም አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል።

ድርጅቶቹ በቴክኖሎጂ ሽግግርና አሠራር ተሞክሮ መቀመሪያ ሆነው እንዲገኙም ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከመደበኛ የልማት ስራዎች ባለፈ በተቆርቋሪነትና ውጤታማነት እንዲገነቡ፤ ሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካም የልህቀት ማዕከል እስከመሆን የዘለቀ ራዕይ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሉሲዎቹ ወደ ናይጀሪያ አመሩ።
Next articleለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ ሥልጠና መሰጠት ተጀመረ።