
ባሕር ዳር:- ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶችን ወደ አመራር ሰጪነት ቦታ ለማምጣት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሚኮ ገልጿል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ እንዳሉት ለተከታታይ 5 ዓመታት በሴቶች የለውጥ አመራር ላይ ሥልጠና ለመሥጠት እየተሰጠ መኾኑን ነግረውናል፡፡
ሴቶችን ወደ መሪነት ለማምጣት እና ውጤታማ መሪ ለማድረግ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሴቶች የአመራር ሥልጠና መውሰዳቸውን ነው ያሥገነዘቡት፡፡ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በመጣው ሴቶችን የማብቃት ኢንሸቲቨ ላይ በመመስረት ወደ 30 የሚኾኑ ሴቶች ሥልጠና ወሥደው ብቁ አመራር ስለመኾናቸውም ገልጸዋል፡፡
ሴቶችን ወደ አመራር ሰጭነት የማምጣቱ ጉዳይ በክልሉ ምክር ቤት ጭምር ትኩረት የተሰጠው ስለመኾኑም ተናግረዋል። በክልሉ በ2012 ዓ.ም በሕግ ተርጓሚው አካል ውስጥ 1 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የሴቶች ተሳትፎ አሁን ላይ 13 ነጥብ 3 መድረሱን ኀላፊዋ ጠቁመዋል። በዞን ደረጃ ከነበረበት 18 በመቶ ቀንሶ አሁን ላይ 16 በመቶ መድረሱን የተናገሩት ኀላፊዋ በወረዳ ደረጃ ከ26 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 29 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡
ከሥራ አሥፈጻሚ አካላት አኳያ በክልል ደረጃ በ2012 ዓ.ም ላይ ከነበረበት 20 በመቶ ቀንሶ አሁን ላይ 17 በመቶ መድረሱን ነግረውናል፡፡ በዞን ደረጃ ደግሞ 26 የነበረው የሴቶች ተሳትፎ 23 በመቶ ፣ወረዳ ላይ ደግሞ 24 በመቶ የነበረው ተሳትፎ ወደ 21 በመቶ ዝቅ ብሏል ብለዋል፡፡
በክልል ደረጃ ያለው የሴቶች ተሳትፎ ሲታይ በክልል ደረጃ 36 በመቶ ተሳትፎ ሲኖራቸው በብሔረሰብ አሥተዳደር ደረጃ 44 በመቶ ፣ በወረዳ ምክር ቤት ላይ 47 በመቶ ተሳትፎ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ ምጥን እንዳሉት የሴቶች ተሳትፎ እያደገ ነው ቢባልም ባለፈው ዓመት ግን ተሣትፏቸው ቀንሶ ታይቷል።
ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ ለዚህም ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አሁን ላይ ክልሉ የአመራር ማዋቀርን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ወይዘሮ ምጥን ሴቶች የሚገባቸውን ቦታ ያገኛሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው ያስረዱት።
ይህም እንዲሳካ ቢሯቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!