“የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ታሪክን እና ቅርስ ማቆያ ማእከልን ለመክፈት ለተደረሰው ውሳኔ መንግሥት ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል” አምባሳደር ተፈሪ መለሰ

22

ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ሦስት ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደምና በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካዊያንና ሌሎች የጥቁር ሕዝቦች

በለንደን የኢትየጵያ ኤምባሲ ሲያካሂዱት የነበረው ተከታታይ ምክክር በኢትየጵያ የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ፣የቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል ለመገንባት ሙሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የማእከሉ መሥራች አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት ማእከሉን ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ቀንዲል በኾነቸው ኢትዮጵያ ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ ታሪካዊና ትክክለኛ ነው ብለዋል።

የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም እሰከ አሁን በተደራጀና ወጥ በሆነ ተቋም አደራጅቶ ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ በቂ ሥራ አልተሠራም ብለዋል፡፡ መንግሥት ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ በየዘመኑ ለአፍሪካ ሕዝቦች ነጻነት ትግል ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን በማስታወስ የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ታሪክን እና ቅርስ ማቆያ ማእከልን ለመክፈት ለተደረሰው ውሳኔ ሕጋዊ በማድረግ ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

የሰው ልጅ ጥንታዊ መገኛ፣ ለዓለም ቅርስና ታሪክ አስተዋጽኦ ሚናዋ ከፍ ያለ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነቸው ኢትዮጵያ ይህ ማእከል መመስረቱ ለአዲሱ ትውልድ የነጻነት ፣ ችግርን የመቋቋምና
በአንድነት አቅምን የማሳደግ ስልት ምን እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠሪያ ነው ይሆናል ብለዋል፡፡

ማእከሉ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የምርምር ተቋም ፣ ትውልዶች ሊማሩባቸው የሚችሉ ቅርሶች ማሳያ ፣የቀደሙት የነጻነት ታጋዮች ትእግስትን የተላበሰ ጽኑ መንፈሳቸውን ማንፀባረቂያ፣ ቁርጠኝነታቸውን እንዲሁም
ያሳለፏቸውን ታሪኮች መነሻ በማድረግ አዲሱ ትውልድ አንድነትን እና ጽናትን የሚማርባቸው እንዲሆን ተደርጎ ይቀረጻል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለማእከሉ ምስረታ ለሦስት ዓመታት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሳያቋርጡ በመገኘት ሲሟገቱ ለነበሩ ከፍተኛ ምሁራንና ይህ ጥረት ሰምሮ ለማየት ያልተቋረጠ ድጋፋቸውን ላደረጉ የማኅበረሰቡ አበላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ስፔሻሊስትና ደራሲ ሮቢን ዎከር በበኩላቸው ከድህረ ቅኝ አገዛዝ በኋላ ያለው የጥቁር ሕዝቦች ላይ ያተኮረ ትርክት እጅግ የተዛባና በረቀቀ መልክ የበታችነት ስሜት ለማጎልበት የታቀደ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ግን ጥቁር ምሁራን በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ ሥነ ልቦና መላበስ ለጥቁር ሕዝቦች ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህን የጥቁር ሕዝቦች በራስ የመተማመን ሥነ ልቡና ለማጎልበት ቅድመ ቅኝ አገዛዝ የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክና ቅርስ መመርመር የሚያስችል ማእከል አዲስ አበባ ላይ መመስረት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለማእከሉ ሕጋዊ ዕውቅና መስጠቱ ሊያስመሠግነው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መድረኩና ከማመቻቸት ጀምሮ እንደ አንድ የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል አካል ኾኖ አቅጣጫና መስመር በማስያዝ ረገድ ለተጫወተው ሚናም ታላቅ ምሥጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የቡድኑ አስተባባሪ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ጸጋዬ ጫማ ቡድኑ የማእከሉን ምስረታ ለማቀላጠፍ ወደ አዲስ አበባ በርካታ አባላቱን በመያዝ መጓዙን እና ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል። በመጪው ታህሳስ በአፍሪካ ኅብረት በይፋ የኅብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ሥራውን በይፋ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ኤምባሲው ለዚህ አላማ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገ በመኾኑ ሊመሠገን ይገባዋል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኤል ክላሲኮ በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
Next article“ሴቶች ወደ አመራር ሰጪነት ቦታ እንዲመጡ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው” የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ