መርሕ የጣሱ ተጫዋቾች መቀጣታቸው ተሰማ።

47

ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የእግር ኳስ ማኀበር ፊፋ “የስፖርት ማዘውተሪያዎች መዝናኛ እንጅ የመቋመሪያ ሥፍራዎች አይደሉም” የሚል መርህ አለው። በፊፋ ሕግ መሠረት አንድ የእግር ኳስ ተጫዋች በምንም መልኩ ሲቆምርም ኾነ ሲያቋምርም ከተገኜ እንደሚቀጣ በግልጽ ተደንግጓል።

የየሀገራቱ የእግር ኳስ ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች የመተዳደሪያ መርኾዎች ደግሞ የተቀዱት ከፊፋ ስለኾነ መርኾዎችን የማክበር ግደታ አለባቸው። በዚህም መሰረት ሰሞኑን የጣልያን የእግር ኳስ ማኅበር ሳንድሮ ቶናሊ የተባለው ጣልያናዊ የኒው ካስትል ዩናይትድ ተጫዋች ቀጥቶታል። ፌዴሬሽኑ ተጫዋቹን ለ10 ወራት ወደ እግር ኳስ ሜዳ ዝር እንዳይልና ኳስም እንዳይነካ ቀጥቶታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። ምክንያቱ ደግሞ ለኤሲ ሚላን በሚጫወትበት ወቅት በህቡዕ በእግር ኳስ ሲቋመር እና ሲያቋምር ስለተደረሰበት ነው። ሳንድሮ ቶናሊ እና ክለቡ የተዋዋሉት ደግሞ ተጫዋቹ ቋሚ ተሰላፊ ሲኾን ሙሉ ደመወዝ ሊከፈለው ነው።

ከተቀያሪ ወንበር እየተነሳ የሚሰለፍ ከኾነ ግን ከደመወዙ ሁለት በመቶ ሊቀነስበት ተስማምተዋል። በጉዳትና በካርድ ከጨዋታ የሚርቅበትን ሳይጨምር በራሱ ጥፋት ከቡድኑ ስብስብ ውጭ ሲኾን ደመወዝ እንደማይከፈለው በፊርማው አረጋግጧል። በመኾኑም ተጫዋቹ ለ10 ወራት ኳስ እንዳይነካ የተቀጣ ስለኾነ ደመወዝ አያገኝምና በእጅጉ ይጎዳዋል ነው የተባለው።

ሌላው የተቀጣው ተጫዋች የአስቶንቪላው ኒኮሎ ዛኒዮሎ ነው። ተጫዋቹ ጣሊያን ውስጥ በሕገ ወጥ የዲጅታል ውርርድ በመሣተፉ ምርመራ እየደረገበት መኾኑም ተዘገቧል። ከቅጣትም አያመልጥም ሲል ዩሮ ስፖርት ዘግቧል።

የጁቬንቱሱ አማካይ ተጫዋች ኒኮሎ ፋጊዮሊም መቋመሩ በሰነድና በተንቀሳቃሽ ምስል በመረጋገጡ የጣልያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሰባት ወር ቅጣት አከናንቦታል።
“አተርፍ ባይ አጉዳይ” አትሉም?

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ።
Next articleኤል ክላሲኮ በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።