የእግር ኳስ ባላንጣነት መለኪያው “ኤል ክላሲኮ”

50

ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እግር ኳስ የሰላም ስፖርት ነው። ፉክክሩ ፣ እልሁ እና ባላንጣነቱ በ90 ደቂቃ ሜዳ ላይ የሚጠናቀቅ ቢኾንም ነገር ግን በአንዳንድ ግጥሚያዎች ይሄ አይሠራም። ኤል “ክላሲኮ”ሪያል ማድሪድን ከባርሴሎና የሚያገናኘው ጨዋታ ለዚህ ሀሳብ ጥሩ ምሳሌ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሦስት ነጥብ ከማግኘት እና ከማጣትም በላይ የታሪክ ፣ የማንነት እና የሀገር ወዳድነት ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል።

ሪያል ማድሪድ የስፔንን አንድነት አጥብቀው በሚፈልጉ እና ቀደም ባለው የሀገሪቱ ታሪክ የበላይነት ነበራቸው በሚባሉ ስፔናዊያን ይደገፋል።

በአንፃሩ ባርሴሎና ካታሎኒያ የምትባል የስፔንን ግዛት ይወክላል ፤ ከስፔን የመገንጠል የበረታ ጥያቄ የሚነሳበት አካባቢ ሲኾን ነጻ የመኾን ሃሳባቸውን በየጊዜው ሥልጣን በሚይዙ መሪዎች በጉልበት እንደተነጠቁ ያምናሉ።

ይሄን ቅሬታቸውን እና ተነጠቅን የሚሉትን ማንነታቸውን የሚገልጹበት እና ራሳቸውን ለዓለም ለማሳየት የሚጠቀሙበት ብቸኛ መንገድ ክለባቸው ባርሴሎናን ነው። ባርሴሎና ባሕል ፣ ቋንቋ እና ማንነት ነው ለካታሎኒያ ሰዎች።

በሌላ ወገን ባርሴሎና የስፔንን አንድነት በማይፈልጉ እና ስፔንን ለመከፋፈል በሚያሴሩ አካላት የሚደገፍ ነው የሚል ሀሳብ ይነሳል። ስለዚህ ለስፔን እና ስፔናዊያን አንድ መኾን በማሰብ ሪያል ማድሪድን ይደግፋሉ።

በእነዚህ አና ሌሎች ምክንያቶች የሁለቱ ክለቦች አንዱ አንዱን ማሸነፍ ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል። ሦስት ነጥብ ከማግኘት በላይ በኳስ አሸናፊነት ካባ የፓለቲካ እና የአሰተሳሰብ ልዕልናን ለማሳየት ጭምር በእግርኳስ ፍልሚያ ያካሂዳሉ።

ባርሴሎና ሲያሸንፍ የካታሎኒያ ነጻ መኾን ሃሳብ ያሸንፋል ፤ በተቃራኒው ማድሪዶች ሲያሸንፉ ስፔን በአንድነቷ ትቀጥላለች የሚለው ሃሳብ ገዝፎ ይታያል።

እናም የሁለቱ ክለቦች የርስ በርስ ግጥሚያ ተጠባቂ እና እልህ አስጨራሽ ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል።

በፊሽካ ተጀምሮ በጥይት ተኩስ የተጠናቀቀ የሁለቱን ክለቦች ግጥሚያ ታሪክ መሰነዱንም ሲቢሲ ስፖርት የተሰኘ የመረጃ ምንጭ አትቷል።

በስፔን ብቻ ሳይኾን በአውሮፓም ገናናነታቸውን ያስመሰከሩት ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ተቀራራቢ የርስ በርስ መሸናነፍ ታሪክ አላቸው።

ሪያል ማድሪድ 102 ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና 100 ጊዜ ባለድል ኾኗል ፤ 52 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

የ2023/24 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው የኤል ክላሲኮ ግጥሚያ ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ቀን 11 ሰዓት ከ15 ላይ ይካሄዳል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰቆጣ ከተማ ሱሰኝነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት ያለመ የሩጫ ውድድር ተካሄደ።
Next articleፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ።