“ቦርከና መቀነቷ፣ ሐረጎ ጉልላቷ”

236

በዙሪያ ገባዋ ያሉ ኮረብታዎች ውበትን ይሰጧታል፣ ግርማን ያላብሷታል፣ የተዋበውን የተፈጥሮ ካባ እንደለበሱ በክብር ያጎናጽፏታል። መወደድ አይለያትም፣ ፍቅር አይጠፋባትም፣ አንድነት አይቀዘቅዝባትም፣ ኢትዮጵያዊነት ይጎላባታል፣ ፍቅር ከእነ ግርማው ይኖርባታል፣ አብሮነት ከእነ ሞገሱ ይታይባታል። ደግነት ቤቱን ሠርቶባታል፣ ከራስ በላይ ማሰብ መሠረቱን አጸንቶባታል።

ብዙዎች ይወዷታል፣ ከአራቱም ንፍቅ እየመጡ ይሰባሰቡባታል፣ በፍቅር ይኖሩባታል፣ በአንደነት ይደምቁባታል፣ በአብሮነት ያጌጡባታል፣ በኢትዮጵያዊነት መልካም ግርማ ይንቆጠቆጡባታል፣ አሸብርቀው ይታዩባታል። በዚያች  ምድር እንኳን ደህና መጣህ እንጂ ከየት መጣህ አይታወቅባትም፣ ወገን አይለይባታም፣ ሃይማኖት አይቆጠርባትም፣ አንደኛው የሌላኛውን ያከብራል፣ ሰውነትን ከሁሉ አልቆ በፍቅር ይኖራል እንጂ።

ቦረከና እንደ መቀነት ሸብ አድርጎ አሳምሯታል፣  በመካከሏ እያለፈ ያማረች የተዋበች አድርጓታል።   ቦርከና  ለእርሷ ወንዝ ብቻ አይደለም ውኃ የምትቀዳበት፣  ቦርከና ውበቷ ነው ውበትን የምትጨልፍበት፣ ቦረከና ቅኔ ነው የምትቀኝበት፣ ቦርከና ትዝታዋ ነው የትናንትን ዛሬ ላይ የምታይበት፣ ቦርከና ተስፋዋ ነው ነገን በአሻገር የምትመለከትበት፣ ቦርከና የመወደዷ ካባ ነው ግርማን የምትላበስበት፣ ቦርከና መንገዷ ነው ከዘመን ዘመን የምትሸጋገርበት፣  ቦርከና የፍቅር ጓሮዋ ነው የመዋደድን ችግኝ የምትተክልበት፣ ቦርከና አትክልቷ ነው የፍቅርን ፍሬ የምትለቅምበት፣  ቦርከና ያማረ መቀነቷ ነው  በወገቧ ሸብ አድርጋ የምታጌጥበት።  ቦርከናን ያነሱ ያነሷታል፣ ስለ እርሱ የተቀኙ ይቀኙላታል፣ ስለ እርሱ ያስታወሱ ያስታውሷታል። ስለ እርሱ ያዜሙ ያዜሙላታል።

ለዚያም  ይመስላል ከያኒው  “ውበቷ እንደዥረት ቦርከና ላይ ሲፈስ
እኔ  መች አየሁት እዚያው ስመላለስ” ያሉላት። እርሷ ውበቷ ከቦርከና ጋር አብሮ ይፈስሳል፣ ፍቅሯም ይጎርፋልና።
                       
ሐረጎ እንደ ጉልላት ውበትን ሰጥቷታል፣ እንደ ዘውድ ግርማን አላብሷታል፣ እንደ አማረ ካባ መወደድን ደርቦባታል። እንደ ተዋበ  የራስጌጥ ከውበት ላይ ውበት ጨማምሮላታል።  እርሷ ታድላለች፣ እርሷ ተመርጣለች፣ የሰው መውደዱን ተሰጥታለች። ደሴን ግርማ የሰጣት፣ ውበትን ያላበሳት  አዝዋ ገደል ቁልቁል ይመለከታታል። እርሷም ወደ ላይ ትመለከተዋለች፣ በውበቱ ትዋባለች፣ በግርማው ትደምቃለች ኮምቦልቻ።

ያማሩ ሕንፃዎች ሳይሠሩባት፣  ጎዳናዎች ሳይጌጡባት፣ የመንገድ ዳር መብራቶች ሳይንቀለቀሉባት፣ አየር በሰማይ ሳያንዠብባት፣  በቦርከና ወንዝ መሻገሪያ ድልድይ ሳይሠራባት፣  ኢንዱስትሪዎች ሳይስፋፉባት፣ በግራም በቀኝም፣ በፊትም በኃላም ማሽን ሳይጮህባት፣ የባቡር ሐዲድ ገና ሳይታሰብባት አስቀድሞ ዘላኖች ላሞቻቸውን የሚነዱባት፣ ጥጃ እያጠቡ ወተት የሚያልቡባት፣ በሬዎቻቸውን፣ ወይፈን እና ጊደሮቻቸውን የሚያሰማሩበት የዘላኖች መናኸሪያ ነበረች።

በዚያች ረባዳማ  ምድር እንደ ንብ መንጋ የበዙ ላምና በሬዎች፣ ወይፈን እና ጊደሮች፣ በግና ፍየሎች፣  ፈረስና በቅሎዎች ተመላልሰውባታል፣ በለመለመው መስክ አረንጓዴ ሳር ግጠውባታል፣ ለጌቶቻቸው እሸትና ወተት ሰጥተውባታል፣ እረኞች በግሬራቸው የጊደር ወተት እየተጎነጩ  ተመላልሰውባታል፣ ዓለም አሳልፈውባታል። ደጉን ዘመን፣ መልካሙን ገዜ  አይተውባታል።

ስለ ምንስ? ኮምቦልቻ ተባለች። መቼስ ተመሠረተች ብለው የጠየቁ እንደኾነ አበው መልስ አላቸው። ኮምቦልቻ የዛሬውን ስሟን ከማግኘቷ አስቀድሞ ቢራሮ ትሰኝ ነበር። ያን የቀደመውን ስሟን ዛሬም አልረሳችም፣ ቢራሮን የምታስታውስበት ብዙ ነገር አላት። ኮምቦልቻ ተወልደው ያደጉትና ታሪክ የሚናገሩት ጋሽ  ሙሐመድ አሊ ኮምቦልቻ ማለት ሀጣጥ እሾህ፣ የሚጠቀጥቅ፣  የሚያሰምጥ፣ ረግረጋማ ሥፍራ ማለት ነው ይላሉ። ኮምቦልቻ ሜዳማ ረግረጋማ ሥፍራ ናትና ስያሜዋም ከዚያ ተቀዳ ነው የሚሉት።

ከከተማዋ ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ደግሞ ኮምቦልቻ የሚለው ስያሜ ከጣልያን ቃል የተቀዳ ነው ይላል። ” ካምፖሉቺያ” ከሚለው የጣልያን ቃል የተገኘ ነው። ይህም  “መብራት ያለበት ሠፈር” ማለት ነው። ይህም ስም እየቆዬ ኮምቦልቻ ኾነ። በዚህ ስያሜዋ አማካኝነት አመሠራረቷም ከጣልያን ወረራ ጋር ይያያዛል ይላል። ታሪክ ነጋሪው ጋሽ ሙሐመድ ግን ይሄን አይቀበሉም። አንድም ኮምቦልቻ ከጣልያን ወረራ አስቀድማ ነበረች፤ ሁለትም የራሷን ስያሜ የወሰደች እንጂ ከጣልያን የተቀዳ ስያሜ የላትም ይላሉ።

ጋሽ ሙሐመድ ሲነግሩን በቀደመው ዘመን በዚያ ሥፍራ ከዓመት እስከ ዓመት በጤና የሚኖር አልነበረም። ቦታው ውኃ የሚቋትበት ረግረጋማ ነበርና ወባ አይጠፋበትም፣ ወረርሽኝም ይነሳበት ነበርና ለሰዎች ጤና ይነሳ ነበር። ብርድና ውርጭ ይበዛበት ነበር። ይህን ያዩ የሀገሬው ሰዎች
” ማነው የሚረግጠው ኮምቦልቻን በውርጭ
እየቀጠቀጠ ይኾናል ውቃጭ”  በማለት ተቀኝተውላታል።  ስለ ፍቅሯ፣ ስለ ሰው ወዳድነቷ እና እንግዳ አክባሪነቷ ደገሞ ሌላም ቅኔ ተቀኝተውላታል።
” እንዴት ነሽ ኮምቦልቻ የራበው መጉረሻ፣ ያረዘው መልበሻ”  እያሉ ነበር የተቀኙላት። የዘላኖች መናኸሪያ ነበረች፣ የባለፀጋዎችም መገኛ ነች፣ ግን ከቦታዋ አቀማመጥ አንፃር ነዋሪዎቿ በበሽታ ይጠቁባት ነበር።  በዚያች ነጭና ጥቁር የሚያመርቱ ብርቱ ገበሬዎች፣ ላምና በሬ የሚያቀረቡ ዘላኖች ቀን በዚያ ውለው ለአዳር ወደተራራው ተጠግተው ያድሩ እንደነበርም ነግረውናል። ለምን ካሉ በረግረጋማው ሥፍራ ሕመም ይከሰታልና።

ዘመን ዘመንን አስከትሎ ገሰገሰ። ንጉሥ በንጉሥ እየተተካ ሄደ። የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ደረሰ። ምሥጋና ይግባቸው እና ጃንሆይ የኮምቦልቻ ነዋሪዎችን ያሰቃየውን ወባና ሌሎች ወረርሽኞች አስረጩት። እልም ብሎ ጠፋ። ነዋሪዎችም ያለ ስጋት መኖር ጀመሩ ነው ያሉን። ሰውም እየወደዳት፣ ሕዝቡም እየበዛባት መጣ። የላምና የበሬ መንጋ እየነዱ በበሽታ ያልቅባቸው የነበሩ ባለጸጎችም ንጉሥ ኾይ ሺህ ዓመት ይንገሡ እያሉ እያመሰገኑ በፍቅር ኖሩ።

ኮምቦልቻ በጣም ሰፊ ሀገር፣ ረግረጋማ ምድር እየተባለች የኖረች፣  በርካታ ታሪክና ሃይማኖት አዋቂዎች የተወለዱባት፣ ተወልደው ታሪክ የሠሩባት፣ ታሪክም ያስቀመጡባት ናት ይሏታል።  ቢራሮ የሚለውን ስያሜ ይዛ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን፣ በንጉሡ ልጅ አማካኝነት የቀናች ናትም ብለውናል። ምንም እንኳ አመሠራረቷ ቀደም ያለች ቢሆኾንም ድምቀት ያገኘችው ግን ከጣልያን ወረራ ወዲህ እንደኾነም ነግረውናል። ከብት በሥፋት ይረባባት፣ ዘላኖችም ይመላለሱባት ነበር።

ታሪክ አዋቂው እንደነገሩን ስለ እርሷ ታሪክ ሲነሳ ዘጠኝ ወንድማማቾች አብረው ይነሳሉ። እነዚህ ወንድማማቾች ሀገር የሚያቀኑ ነበሩ። ከዘጠኙ ወንድማማቾች መካከል አንደኛው ሼህ ዳውድ ነበሩ። የደሴው ዳውድም ከእርሳቸው ስምና ታሪክ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደኾነ ያነሳሉ። በዚያ ዘመን ቦርከና በአሁኗ ኮምቦልቻ በቀድሞዋ ቢራሮ መካከል አይፈስም ነበር፣ ሼህ ዳውድ በኮምቦልቻ ውኃ አጡ። ውኃም ያገኙ ዘንድ ቦርከናን በዘንግ እየመሩ በአዘዋ ገደል አድርገው ቁልቁል አመጡት። ቦርከናን በኮምቦልቻ መካከል አፍስሰው፣ ለእርሳቸውም ለወንድሞቻቸውም ውኃን አስገኙ ነው ያሉን።

ታሪክ አዋቂው ስለ ኮምቦልቻ አብሮነትና ፍቅር ሲነግሩን ከሌላ ቦታ መጥተህ ኮምቦልቻ  ትኖራለህ፣ በዚያም ከእኔ ወንድም ጋር ብትጣላ፣ እኔ ለወንድሜ አላግዝም የማግዘው ለእንግዳው ነው፣ እንግዳ ይከበራል፣ ፍቅር ይሰጣል፣ አክብሮ አልቆ ይያዛል ነው ያሉን ጋሽ ሙሐመድ። በቀደመው ዘመን ጀመሮ የሀገሬው ባላባቶች ከሌላ ቦታ የመጣን ሰው ይድራሉ፣ ይኩላሉ፣ ሕይወቱን ይመራበት ዘንድም ከእርስታቸው ቆርሰው መሬት ይሰጣሉ። ማዕድ  የሚበላው፣ ቡና የሚጠጣው በአንድ ላይ ነው። መለያየት አይታወቅም ነው ያሉን።

በዚያ ስፍራ የሚደንቅ ነገር ሞልቷል። አበው ምርቱን ከአውድማው ጭነው ሲወስዱ፣ በአውድማው እህል ይተዋሉ፣ ያም አዝመራ ያላዘመሩ፣ ድኅነት የያዛቸው ሰዎች ሲመጡ አፍሰው እንዲወስዱና እንዲበሉ  በማሰብ ነው። እንኳን ሰዉ ከብቶች እንኳን ፍቅር ያውቃሉ ይላሉ ጋሼ። አሁን የአየር ማረፊያ የኾነውን ጨምሮ ብዙዎች የከብት ማገጃ ነበሩ። ጀንበር ልትጠልቅ ስታዘቀዝቅ እረኞች ከፍ ካለ ሥፍራ ወጥተው ” ነይ ነይ” ብለው ሲጣሩ ከብቶች  ከየዋሉበት መሥመር ስርተው ወደ ተጠሩበት አቅጣጫ ይመጣሉ። አንደኛው መንገድ ከጀመረ ሌላኛው አይቀርም። የእረኞችን ጥሪ ሰምተው ይመጣሉ እንጂ።

ሁሉም የጠባቂዎቻቸውን ድምጽ ያውቃሉ። ጠባቂዎቻቸውም ወደ ተጣሩበት ሥፍራ ይጓዛሉ። በፍቅርም ይሰባሰባሉ። ኮምቦልቻ አሁንም ድረስ ፍቅር መልቷል። ከየትም ይምጣ ሁሉም እንደ ቤቱ ይኖርባታል።  ጋሼ ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ እኔ ስወለድ አርባ ጊደሮች ወልደዋል። ጤፍ ሞልቷል፣ ሽንብራ እንኳን ለሰዎቹ ለበሬዎችም ተርፎ ነበር፣ ወተትና ማሩም ለጉድ ነበር ይላሉ ያን የልጅነት ዘመናቸውን ሲያስታውሱ። ኮምቦልቻ ከሚበላ እንስሳ  በስተቀር የማይበላ አይሸጥብሽ ተብላ ሥርዓት የታሰረባት፣ አበው ያሰሩት ሥርዓትም እስከዛሬ ድረስ የሚከበርባት የቃል ኪዳን ከተማ መኾኗንም ነግረውናል።

ዘመን ተሸኝቶ  ሌላ ዘመን መጣ። የደርግ ዘመንም ደረሰ። በዚህም ጊዜ  ኮምቦልቻ ከወትሮው ተለይታ አደገች  ነው ያሉን። እድገቷን አድረው ሲያዪዋት እየጨመረ፣ ባለፀጋዎች እየተሰባሰቡባት አሁን ላይ የኢንዱስትሪ ማዕከል ኾናለች።  ቀደም ሲል የዘላኖች ከተማ የነበረችው  አሁን የኢንደስትሪ ከተማ ናት። አሁን እንደ ቀደሙት ላሞችና በሬዎች ሁሉ የበዙ ኢንዱስትሪዎች አሏት።

በአየር የሚበር፣ በምድር የሚሽከረከር ሁሉ ይከትምባታል፣ በባቡር የሚሰግረውን ለመቀበልም ከጫፍ ደርሳለች፣ ያን ጊዜ ትልቃለች፣ ያን ጊዜ ከውበት ላይ ውበት ትደርባለች፣ ያን ጊዜ በስልጣኔ ትረማመዳለች፣ እርሷ እልፍ ፀጋዎች፣ እልፍ ተስፋዎች አሏትና። ኮምቦልቻ ከወደብ የሚነሳው የሚያርፍባት፣ ነግዶ ለማትረፍ የሚያልመው የሚሰባሰብባት፣ የኢትዮጵያዊነት ብርቱ ገመድ ያለባት የረባዳማ ሥፍራ ከተማ ናት።  በጎዳናዎቿ ተረማምደናል፣ በወንዟ በቦርከና ተሻግረናል፣ ከነዋሪዎቿ ፍቅርን ተቀብለናል፣ መዋደድን ወስደናል፣ ሰላምን አይተናል፣ በሰላምም ተመላልሰናል። ኮምቦልቻ የተወደደች፣ ኮምቦልቻ በተስፋ የተመላች የረግረጋማ ውስጥ ውብ ሥፍራ።

በታርቆ ክንዴ

Previous articleትውልዱ አረጋውያንን ማክበር፣ ማድመጥ እና ችግር ላይ የወደቁትን ደግሞ መደገፍ እንደሚገባ ተጠየቀ።
Next articleከ5 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር በሰቆጣ ከተማ ተካሄደ።